Fana: At a Speed of Life!

ሩሲያ ቦሪስ ጆንሰንን ጨምሮ ሌሎች 10 ከፍተኛ የእንግሊዝ ባለሥልጣናት ወደ ሀገሯ እንዳይገቡ አገደች

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ በዩክሬን ላይ እየወሰደች ያለውን ወታደራዊ እርምጃ በሚመለከት እንግሊዝ በወሰደችው “የጠላትነት አቋም” ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንን ጨምሮ ሌሎች የአገሪቱን ከፍተኛ ባለስልጠናት ወደ ሀገሯ እንዳይገቡ አግዳለች።

የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊዝ ትሩስን ጨምሮ የመከላከያ ሚኒስትር ቤን ዋላስ እና ሌሎች የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የካቢኔ አባላት ወደ ሩሲያ እንዳይገቡ ታግደዋል፡፡

ሩሲያ ውሳኔውን ያሳለፈችው ዩክሬን ላይ ወታደራዊ እርምጃዎችን መውሰዷን ተከትሎ እንግሊዝ የተለያዩ ማዕቀቦችን ሩሲያ ላይ በመጣሏ እንደሆነም የመገናኛ ብዙሃን ዘገባ ያመላክታል፡፡

የሩሲያ መንግስት በመግለጫው÷ እንግሊዝ ሩሲያን ከዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ለማግለል እና ለመቆጣጠር ብሎም ኢኮኖሚዋን ለመጉዳት ያላጤነችውን እርምጃ በግብታዊነት አሳልፋለች፤ በዚህም ተጠያቂነቱን እራሷ እንግሊዝ ትወስዳለች ብሏል፡፡

እንግሊዝ ÷ ሩሲያ እና ዩክሬን የገቡበትን ጦርነት ከማርገብ ይልቅ የጦር መሣሪያዎችን ለዩክሬን በማቅረብ ብሎም በኔቶ በኩል መሣሪያዎች ለዩክሬን እንዲደርሱ በማስተባበር ግጭቱን እያባባሰች ትገኛለች ስትልም ሩሲያ አጥብቃ መውቀሷን ቢቢሲ፣ ዴይሊ ሜይል፣ ፖለቲኮ፣ ዩሮ ኒውስን ጨምሮ የተለያዩ ዓለምአቀፍ የዜና ምንጮች አመላክተዋል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.