Fana: At a Speed of Life!

በጎርጎራ ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት በተለያዩ መስኮች ለሚሰማሩ 104 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጎርጎራ ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት በተለያዩ መስኮች ለመሰማራት ከ3 በሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱ ተገለጸ።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ባለሙያ አቶ አምባቸው አናጋው እንደገለጹት፥ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተጀመረው የጎርጎራ ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ባለሃብቶችን እየሳበ ነው።

ኢንቨስትመንት ፈቃዱ የተሰጠው በአካባቢው የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በሆቴል፣ ቱሪዝምና በሌሎች ተያያዥ ዘርፎች ለመሰማራት ጥያቄ ላቀረቡ 104 ባለሀብቶች መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ፈቃዱ ከተሰጣቸው ውስጥም ወደ 2 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ካፒታል ያስመዘገቡ በውጭ የሚኖሩ 30 ዳያስፖራዎች መሆናቸው ነው የተገለጸው።

ባለሙያው እንዳሉት ፥ ባለሀብቶቹ ከሆቴልና ቱሪዝም፣ ከሪዞርትና ሎጅ ዘርፎች ባሻገር በአሣ እርባታ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በወተትና ወተት ተዋጽኦ ማቀናበር ሥራዎች የሚሳተፉ ናቸው።

ባለሀብቶቹ ግንባታቸውን አጠናቀው በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ሲገቡ ከ24ሺህ ለሚበልጡ ወገኖች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል እንደሚፈጥሩም አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅት ለባለሀብቶቹ የግንባታ ቦታ ለመስጠት በኢንቨስትመንት ኮሚቴዎች እየተካሄደ ያለው የፕሮጀክት ግምገማ እየተጠናቀቀ በመሆኑ በቅርቡ ቦታውን መስጠት ይጀመራል ብለዋል።

በጎርጎራ ለሀገር ፕሮጀክት በተለያዩ የልማት ዘርፎች ለሚሰማሩ ባለሀብቶች 400 ሄክታር ቦታ ከ3ኛ ወገን ነፃ ሆኖ መዘጋጀቱን የምዕራብ ደንቢያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማንዴ ዘሜ ገልጸዋል፡፡

በጎርጎራ ከተማ ለኢንቨስትመንት የተሰጣቸውን ቦታ ላለፉት 11 ዓመታት አጥረው ካስቀመጡ 23 ባለሃብቶች የወሰዱትን ቦታ በማስመለስ ለአልሚ ባለሃብቶች ክፍት ተደርጓል ብለዋል።

የጎርጎራ ከተማን ምቹ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ በጥናት ላይ የተመሰረተ መዋቅራዊ የከተማ ፕላን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ እየተዘጋጀ መሆኑንም አመልክተዋል።

በወተትና ወተት ተዋጽኦ ማቀናበር ለመሰማራት በ187 ሚሊየን ብር ካፒታል የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን የ”ሮዚዮን አግሮ ፕሮሰሲንግ ካምፓኒ” አስተባባሪ አቶ ሳሙኤል ውብነህ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኩባንያው ተመጋጋቢ በሆኑ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በዶሮ እርባታ፣ በሆቴልና የመዝናኛ ሎጅ ተሰማርቶ ለ600 ወገኖች ቋሚና ጊዚያዊ የሥራ እድል ለመፍጠር እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የጎርጎራ ለሀገር ፕሮጀክት የሲቪል ግንባታ ሥራው 90 በመቶ እንደደረሰ መገለጹ ይታወሳል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.