Fana: At a Speed of Life!

ከውጭ በግዢ የገባው የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ በወቅቱ እንዲደርስ ግብርና ሚኒስቴር አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኅብረት ሥራ ማኅበራት ወደ ሀገር ውስጥ የገባውን የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እንዲያደረጉ ግብርና ሚኒስቴር አሳሰበ፡፡

ግብርና ሚኒስቴር በ2014/15 ምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭትን በተመለከተ ከተለያዩ ክልሎች እና የፌደራል ባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ ከተማ ተወያይቷል፡፡

በዘንድሮው ምርት ዘመን ለአፈር ማዳበሪያ ግዥ 650 ሚሊየን ዶላር ዕቅድ ቢያዝም በዓለም አቀፍ ወቅታዊ ክስተቶች ሳቢያ በተፈጠረ የዋጋ መናር የፍላጎቱ ዋጋ ወደ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር እንዳደገ በሚኒስቴሩ የኢንቨስትመንትና ግብዓት ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሳ ገልጸዋል።

በዚህም መንግስት ለአፈር ማዳበሪያ ግዢ ልዩ ትኩረት በመስጠት የ1 ቢሊየን ዶላር የግዢ ወጪ ፈቅዶ ግዥ እንደተፈጸመ እና ወደአገር ውስጥ እየተጓጓዘ እንደሆነ አንስተዋል።

ወደ ሀገር ውስጥ እየተጓጓዘ ያለው የአፈር ማዳበሪያም ÷ አርሶ አደሩ እጅ በወቅቱ እንዲገባ የክልል ባለድርሻ አካላት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

የግል ሰፋፊ እርሻ ባለቤቶች የአፈር ማዳበሪያ ጥያቄ አግባብነት እንዲጤንና በህገ ወጥ መንገድ ለፋብሪካዎች የሚሸጡ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ካሉም እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ሚኒስትር ዴኤታዋ አስጠንቅቀዋል።

መንግስት የሚያስመጣው የአፈር ማዳበሪያ በኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል ለአርሶ አደሩ የሚዳረስ እንጂ ‘ዩሪያ’ የአፈር ማዳበሪያን ለፕላስቲክና መሰል ምርቶች በግብዓትነት ለሚጠቀሙ ፋብሪካዎች የሚውል እንዳልሆነ ገልጸዋል።

የፌዴራል ኅብረት ሥራ ኮሚሽን የሕብረት ሥራ ግብይት ዳይሬከተር ወይዘሮ ይርጋለም እንዬው ÷ኅብረት ሥራ ማኅበራት 98 በመቶውን የአፈር ማዳበሪያ ለተጠቃሚው እንደሚያሰራጩ ገልጸዋል።

ከ70 በላይ ዩኒየኖች እና ከ8 ሺህ በላይ መሰረታዊ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ለዚህ ተልዕኮ ተለይተው ማዳበሪያ ለማሰራጨት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ከትራንስፖርት ጫና ጋር ተያይዞ በስርጭት ረገድ ሂደቱ በሚፈለገው ፍጥነት እየተሳለጠ እንዳልሆነ ገልጸው፣ ችግሩን በመቅረፍ ቅድሚያ ለሚያስፈልጋቸው ቅድሚያ ለማድረስም ከባለድርሻ አካላትጋር እየሰሩ መሆኑንም የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል፡፡

የበጀትና ሎጀስቲክስ ችግር፣ በቂና ጥራት ያለው መጋዘን ያለመኖር፣ የተራዘመ የጨረታ ሂደት፣ የፀጥታችግር፣ የዋጋ ንረትና የባለደርሻ አካላት አለመናበብ በአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች እንደሆኑ በውይይቱ ተነስቷል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.