Fana: At a Speed of Life!

በጦርነትና በግጭት ውስጥ ሆነው ተፈትነዋል ተብለው የተለዩ የ12ኛ ክፍል የማለፊያ ውጤት ያላመጡ ተማሪዎች በዚህ አመት ይፈተናሉ – ትምህርት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) በጦርነት እና በግጭት ውስጥ ሆነው ተፈትነዋል ተብለው የተለዩ እና የ12ኛ ክፍል የማለፊያ ውጤት ያላመጡ በዚህ ዓመት በሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና እንደ መደበኛ ተማሪ ሆነው መፈተን እንደሚችሉ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር፣ ሁሉም ክልሎች እና የከተማ መስተዳድሮች ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር፣ የሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች በሰጡት የጋራመግለጫ÷ የሚመለከታቸውን አካላት በማሳተፍና በማማከር በሁሉም ክልሎች ስምምነት መሰረት ሁለት ውሳኔዎች መወሰናቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡

አንደኛው ውሳኔ፥ ከመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የተገኘው ተጨማሪ የቅበላ አቅም በፍትሃዊነት ለአራቱ ክልሎች በጦርነቱ ምክንያት በተጎዱ ተፈታኞች መጠን ማከፋፈል የሚል ነው፡፡

ሁለተኛው ውሳኔ ደግሞ በጦርነትና ግጭት ውስጥ ሆነው ተፈትነዋል ተብሎ በተላኩት አካባቢዎች ውስጥ የተፈተኑና በዚህዓመት ማለፊያና ወደ መንግሰት የኒቨርሲቲ መግባት ያልቻሉት ተማሪወች በ2014 ዓ.ም. በሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናእንደመደበኛ ተማሪ ሆነው መፈተን እንዲችሉ የሚሉ ናቸው፡፡

በጋራ መግለጫው እንደተመላከተው÷ በ2013 ዓ.ም ካለፈው ዓመት አኳያ የተፈታኞች ቁጥር መብዛት፣ ፈተናው በሁለት ዙር መሰጠቱ፣ የፈተና እና መልስ ወረቀቶችን በማጓጓዝ፣ ፈተናውን በመስጠት፣ ፈተና ወረቀቶች ፈተናዎች እየተሰጡ ባሉበት እና ከመሰጠታቸው በፊት በማህበራዊ ሚዲያ መዘዋወራቸው፣ የፈተና መልስ አለን የሚሉ ወገኖች በማህበራዊ ሚዲያ መብዛት ወዘተ ችግሮች አጋጥመው አልፈዋል፡፡

የፈተና ወረቀቶች ወጥተዋል ተብለው ከተጠቀሱ የትምህርት ዓይነቶች ጋር ተያይዞ የመጨረሻ ድምዳሜ ላይ ለመድረስና መፍትሄ ለማስቀመጥ የግድ የፈተና እርማት፣ ውጤት ጥንቅርና ትንተና ማድረግ ተገቢ ስለነበር ይሄው ሂደት ተጠብቆ የሥነ ዜጋ ትምህርት ውጤት መጋሸብ በሁሉም አካባቢዎችና ትምህርት ቤቶች በማጋጠሙ ምከንያት ውጤቱ እንዲሰረዝና ለዩኒቨርስቲ መግቢያ እንደማያገለግል የካቲት 16 ቀን 2014 ዒም በትምህርት ምዘናና ፈተና አገልግሎት በኩል ተማሪዎችና ወላጆች እንዲያውቁት መደረጉንም መግለጫው አውስቷል።

በትምህርት ዓይነትና በክልሎች መካከል ያለው ልዩነት እንዳለ ሆኖ÷በሁለት ዙር ፈተና ከወሰዱ 598 ሺህ 679 ተማሪዎች ውስጥ 45 ከመቶ ወይም 268 ሺህ 336 ተማሪዎች በተፈተኗቸው ፈተናዎች አማካይና ከዚያ በላይ ውጤት መስመዝገባቸው ተመላክቷል።

ይህም ማለት 268 ሺህ 336 ተማሪዎች በተለያዩ አማራጮች ከፍተኛ ትምህርት (የዩኒቨርሲቲ ትምህርት) መከታተል ይችላሉ ማለት እንደሆነም አስረድቷል፡፡

በተያያዘም ሁሌም እንደሚደረገው መንግስት ባሉት መደበኛ ዩኒቨርሲቲዎች ማስተናገድ የሚችለውን ያህል ተማሪዎች ነፃ ሊባል የሚችል ስኮላርሽፕ እንደሚሰጥ ጠቅሶ፥ ይህ የሚወሰነው በዋናነት በመንግስት ዩኒቨርስቲዎች የማስተናገድ አቅም ሲሆን÷የተገኘው የመቀበል አቅም 152 ሺህ 14 ሆኖ ከቀደመው ዓመት (147 ሺህ) ጋር ሲነፃፀር የተወሰነ ጭማሪ አሳይቷል ብሏል።

የተመዘገበው የቅበላ አቅም ጭማሪ እንደተጠበቀ ሆኖ የመንግስት ዩኒቨርስቲ መግቢያ መቁረጫ ነጥብ ተወስኖ ከተፈተኑት 598 ሺህ 679 ተማሪዎች ውስጥ በመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ቅበላ የሚያገኙት25 ከመቶ ገደማ መሆናቸውንም አውስቷል።

መጋቢት 5 ቀን 2014 ዓ.ም የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ቅበላ አቅምና ምደባ ለማግኘት መመዝገብ ያለበትን ነጥብ አስመልክቶ ውሳኔና መግለጫ ከተሰጠ በኋላ፥ የተለያዩ አካላት ከመቁረጫ ነጥብና አጠቃላይ ከፈተና እርማትና ውጤት ማሳወቅ ጋር ተያይዞ ባሉ ጉዳዮች ላይ ጥያቄ በማንሳታቸው የማወያየት፣ ተጨማሪ መግለጫ የመስጠት፣ ጉዳዩን ይበልጥ መረዳትና መገንዘብ ለፈለጉ አካላት ማብራሪያ ሲሰጥ ቆይቷልም ብሏል መግለጫው።

በተሰራው ሥራም ተፈጥረው የነበሩ ብዥታዎችንና ቅሬታዎች በተመለከተ÷ የፈተና እርማት በተመለከተ ያጋጠመ ችግር አለመኖሩ፣ ውጤት ማሳወቅን በተመለከተ በሁለት ዙር ፈተና በመሰጠቱ አጋጥሞ የነበረው ችግር መታረሙን፣ በመጀመሪያው ዙር ተፈታኞች በስነ ዜጋ ትምህርት ካጋጠመው በስተቀር ሌሎች የትምህርት ዓይነቶችን ውጤት ውድቅ ለማድረግ አሳማኝ የውጤት ትንተና አለመኖሩን፣ በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ቅበላ የሚያገኙትን በተመለከተ በቀደሙት ዓመታት ከመሰናዶ ትምህርት በኋላ ከሚፈተኑት ጋር በማነፃፀር የተፈጠረ አለመረዳት መኖሩ የሚሉት ስምምት ላይ ከተደረሰባቸው ነጥቦች ዋና ዋናዎቹ መሆናቸው ተብራርቷል፡፡

በአብዛኛዎቹ ክልሎች የውጤት መቀነስ ቢያጋጥምም÷ በጦርነትና በፀጥታ መጓደል ምክንያት አንዳንድ አካባቢዎች በተለየ ሁኔታ በተለይ ደግሞ አፋር፣ አማራ፣ ኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ክልሎች በልዩነት ማየት የሚቻልበት እድል ካለ ቢታይ የሚሉ አስተያየቶች ቀርበው ትምህርት ሚኒስቴር አማራጮች እንዲያቀርብ ከስምምነት ተደርሶ አማራጮችን የማየት ሥራ ተሰርቷል።

በዚህ መሰረት ትምህርት ሚኒስቴር በስራ ላይ ያሉ 43 ዩኒቨርሲቲዎች ይህን ችግር ለመፍታት የመጨረሻ አቅማቸውን አሟጠው በመጠቀምና ትግራይ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች መጥተው በጊዜያዊነት ከተመደቡት ውስጥ በቅርቡ ጨርሰው የሚመረቁትን ታሳቢ በማድረግ ተጨማሪ የቅበላ አቅም ማግኘት ተቸሏል፡፡

በተጨማሪም አራቱም ክልሎች (አፋር፣ አማራ፣ ኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል-ጉሙዝ) በፈተና ወቅት ተማሪዎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ተፈትነዋል ብለው የሚያስቧቸውን ዞኖች/ወረዳዎች/ ትምህርት ቤቶች እና በየትምህርት ቤቶቹ የተፈተኑትን ተማሪዎች ለይተው እንዲያሳውቁ ተደርጓል፡፡

በምንይችል አዘዘው እና አወል አበራ

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.