Fana: At a Speed of Life!

ከበዓሉ ጋር በተያያዘ ህብረተሰቡ የእሳትና የኤሌክትሪክ አደጋ እንዳይከሰት ጥንቃቄ እንዲያደርግ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የፋሲካ እና የኢድ-አልፈጥር በዓላትን አስመልክቶ ህብረተሰቡ ከእሳት እና ድንገተኛ አደጋዎች ራሱን እንዲጠብቅ አሳሰበ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰለሞን ፍስሐ ዛሬ በሰጡት መግለጫ÷ ህብረተሰቡ ከበዓሉ ጋር በተያያዘ ምግብ በሚያበስልበት ወቅት በኤሌክትሪክ አጠቃቀም፣ በሲሊንደርና በቡታጋዝ ምክንያት ሊከሰት ከሚችል ድንገተኛ የእሳት አደጋ ራሱን እንዲጠብቅ ጠይቀዋል።

ህብረተሰቡ መጪውን የፋሲካና የኢድ -አልፈጥር በዓላትን ሲያከብር የኤሌክትሪክ ፍሰትን በመቆጣጠር የአደጋ ስጋቶችን ከመነሻቸው በመለየት አስፈላጊውን ሁሉ ጥንቃቄ አስቀድሞ ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡

ተጨማሪም ከበዓላቱ ጋር በተያያዘ የሰዎች እንቅስቃሴ ሊበራከት ስለሚችል ህብረተሰቡ ራሱን ከትራፊክ አደጋ እንዲጠብቅ አሳስበዋል፡፡

ህብረተሰቡ ከበዓላቱ አከባበር ጋር ተያይዞ ከሚያደርጋቸው ጥንቃቄዎች ጎን ለጎን የአደጋ ስጋቶችን ሲመለከትና አደጋ ሲያጋጥም በ939 ነጻ የስልክ መስመር በመደወል በመዲናዋ ከሚገኙ ዘጠኙም ቅርንጫፎች ፈጣን አገልግሎት መጠየቅ ይኖርበታል፤ ለዚህም ተቋሙ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ከሕዝቡ በሚደርሰው ጥቆማ መሠረት እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል፡፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በአዲስ አባባና አካባቢው በአጠቃላይ 377 አደጋዎች ማጋጠማቸውን ገልጸው÷ 251 የእሳት ቃጠሎና 126 ከእሳት ውጪ ያሉ ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ባጋጠሙ አደጋዎችም የ104 ሰዎች ሕይወት ማለፉንና 154 ሰዎች ደግሞ ቀላልና ከባድ የመቁሰል አደጋ እንዳጋጠማቸው  ማብራራታቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

 

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.