Fana: At a Speed of Life!

ትናንት ምሽት በመላ ሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ሀይል ለምን ተቋረጠ?

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ትናንት ምሽት ላይ በመላው ሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ሀይል ተቋርጦ ነበር።

በዕለቱ ከሰዓታት በኋላ የተወሰኑ አካባቢዎችም የኤሌክትሪክ ሀይልን ዳግም መልሰው ያገኙ ሲሆን፥ የተወሰኑ አካባቢዎች አሁንም ሀይል እንደተቋረጠባቸው ነው።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን በሀይል መቋረጡ ዙሪያ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳስረዱት፥ የሀይል መቋረጡ ከጊቤ 2 የሀይል ማመንጫ ከሚነሳው የሀይል ማስተላለፊያ መስመር ጋር የተያያዘ ነው።

ከጊቤ 2 የሀይል ማመንጫ የሚነሳው እና ወደ ሰበታ እና ወደ ሶኮሮ የሚሄደው 400 ኪሎ ቮልት ሀይል ተሸካሚ ከፍተኛ መስመር በአካባቢው በነበረ ንፋስ በቀላቀለ ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት ችግር ገጥሞት ነበር።

በዚህ ምክንያት በዚህ መስመር የሚያልፈው ሀይል ከጊቤ 3 ተነስቶ ከወላይታ ሶዶ ወደ ገላን ወደሚገባው መስመር ሀይሉን መላኩን ይናገራሉ።

በዚህ ወቅት ከጊቤ 3 የሚነሳው እና ብዙሃኑን የሀገሪቱን የሀይል ፍላጎት የሚያሟላው መስመር ይህ ሀይል ሲመጣበት ራሱን በራሱ እንደተቋረጠ ነው ያስረዱት።

ሰዓቱ ከፍተኛ ሀይል ጥቅም ላይ የሚውልበት በመሆኑም ከቀሩት የሀይል ማመንጫዎች የሚገኘው ሀይል ፍላጎቱን ማሟላት እንዳልቻለ እና አብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል አቅርቦቱ እንደተቋረጠ ገልፀዋል።

የችግሩ ምንጭ በመታወቁ እና ማስተካከያ በመደረጉም እስከ ንጋቱ 11 ሰዓት ድረስ ሀይል ተቋርጦባቸው ከነበሩ አካባቢዎች መካከል አብዛኛዎቹ አገልግሎቱ እንደተመለሰላቸው አቶ ሞገስ ተናግረዋል።

ችግሩ ሙሉ በሙሉ ቢቀረፍም የአዳንድ መስመሮችን ደህንነት የማረጋገጥ ስራ እየተከናወነ በመሆኑ በተወሰኑ አካባቢዎች አሁንም ሀይል እንዳልመጣ እና ደህንነት የማረጋገጡ ስራ እንደተጠናቀቀ አገልግሎቱን እንደሚያገኙ ገልፀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.