ሴናተር ኪም ጃክሰን በህወሓትና ደጋፊዎቹ የሀሰት መረጃ በመታለል ኢትዮጵያ ላይ አግባብ ያልሆነ አቋም በመውሰዳቸው ይቅርታ ጠየቁ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ የጆርጂያ ሴናተር ኪም ጃክሰን፥ በህወሓትና ደጋፊዎቹ ፕሮፖጋንዳና የሀሰት መረጃ በመታለል አለአግባብ ኢትዮጵያ ላይ ለወሰዱት የተሳሳተ አቋም ይቅርታ ጠየቁ፡፡
ሴናተሯ ይቅርታ የጠየቁት በአሜሪካ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አባላት ባዘጋጁት የውይይት መድረክ ላይ ነው፡፡
በአሜሪካ የጆርጂያ ሴናተር ኪም ጃክሰን በተለያዩ የማኅበራዊ ትሥሥር ገጾች እና በኢሜል በሚደርሱኝ መልዕክቶች ኢትዮጵያውያን ከትግራይ ህዝብ ጋር ምንም ዓይነት ችግር እንደሌለባቸው አሳውቀውኛል፤ ወንድሞቻችን፣ እህቶቻችን እና ጓደኞቻችን ናቸው ሲሉም በተደጋጋሚ በኢሜል ገልጸውልኛል ብለዋል፡፡
እኔም አሁን የደረስኩበትን እውነታ ከግምት ሳላስገባ ቀድሞ በደረሰኝ የህወሓት ደጋፊዎች የሀሰት መረጃ ብቻ የተሳሳተ አቋም ይዤ ነበር ብለዋል ሴናተሯ፡፡
ለፈጠርኩት ስህተትም ሙሉ ኃላፊነት ወስጄ ለማረም እሠራለሁ፤ የኢትዮጵያ መንግስትንና ህዝቡን ይቅርታ እጠይቃለሁም ነው ያሉት፡፡
እኔና ሌሎች ሴናተሮች እና ጓደኞቼ በህወሓት ፕሮፖጋንዳ ተሳስተናልም ብለዋል።