3 የኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለሙያዎች ጉቦ ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን ፖሊስ ገለጸ
አዲስ አበባ፣ሚያዚያ 10፣2014 (ኤፍ ቢሲ) በመዲናዋ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በህገ-ወጥ መንገድ የግለሰብን የኤሌክትሪክ ቆጣሪ ቆርጠው ኃይል አቋርጠዋል የተባሉ 3 የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለሙያዎች ጉቦ ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለፀ።
በክፍለ ከተማው ወረዳ 6 ልዩ ቦታው ጨው በረንዳ አካባቢ ተጠርጣሪዎቹ ወደ ግል ተበዳይ መኖሪያ ቤት በመምጣት ቆጣሪ ልናነብና ልንመረምር ነው ካሉ በኋላ የኤሌክትሪክ ቆጣሪውን አይተው 33 ሺህ ብር እንደቆጠረ ለግል ተበዳይ ነግረዋቸዋል ነው የተባለው፡፡
የግል ተበዳይም ያልተጠቀሙበትን ፍጆታ እንደቆጠረባቸውና ከአቅማቸው በላይ መሆኑን ሲያሥረዷቸው ከተፈቀደልህ በላይ ሃይል ጨምረህ ተጠቅመሃል በማለት የሁለት ቆጣሪዎች ሃይል እንዲቋረጥ ማድረጋቸውን የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ወንጀል ምርመራ ማስተባበሪያ ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር እሱባለው ጌትነት ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ባለሙያዎቹ 15 ሺህ ብር እጅ መንሻ ጉቦ ከሰጧቸው እንደሚያስተካክሉላቸው ለግል ተበዳይ ነግረው ገንዘብ መጠየቃቸውን የጠቀሱት ምክትል ኢንስፔክተሩ የግል ተበዳይም ይህን ያህል ገንዘብ እንደሌላቸው እና 10 ሺህ ብር እንዲያደርጉላቸው ተደራድረው ከጠየቋቸውም ገንዘብ ውስጥ 5 ሺህ ብር ሲቀበሉ ቀደም ብለው ጉዳዩን ለፖሊስ አሳውቀው ስለነበር ከነ ገንዘቡ እጅ ከፍንጅ ሊያዙ መቻላቸውን አብራርተዋል፡፡
ህዝብ እና መንግስት የጣሉባቸውን ኃላፊነት ወደጎን በመተው ህብረተሰቡን የሚያማርሩ ግለሰቦችን ለህግ አጋልጦ በመስጠት ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ የሁላችንም ኃላፊነት ነው ሲሉ የግል ተበዳይ መናገራቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡