Fana: At a Speed of Life!

ሩሲያ በዩክሬን ዶንባስ ግዛት መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ከፈተች

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) ሩሲያ በዩክሬን ዶንባስ ግዛት መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ መክፈቷ ተገለፀ።

የሩሲያ የመካላከያ ሚኒስቴር ሞስኮ ትናንት ማምሻውን በዩክሬን መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ጥቃት መክፈቷን አስታውቋል።

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪም ሩሲያ በዶንባስ ግዛት አዲስ ጥቃት ከፍታብናለች ብለዋል።

ሩሲያ ሌሊቱን ሙሉ በዓየር ኃይል፣ በሚሳኤል እና መድፍ ታግዛ በፈጸመችው ሰፊ ጥቃት በዩክሬን ወታደራዊ ኃይል ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ማድረሷን የሀገሪቷ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ጥቃቶቹ ዒላማ ያደረጉትም ካርኪቭን፣ ዛፖሮዢያን፣ ዶኔስክን እንዲሁም በማይኮላይቭ ወደብ የምትገኘው ዲፕሮፔትሮቭስክ ከተማ ንመሆኑ ነው የተመላከተው፡፡

በጥቃቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዒላማዎችን ሩሲያ መምታቷን መከላከያ ሚኒስቴሯ አስታውቋል፡፡

ሌሊት በተፈጸመው መጠነ ሰፊ የሚሳዔል ጥቃት፥ አምስት የዩክሬንን ወታደራዊ የዕዝ ማዕከላት ፣ አንድ የነዳጅ ዴፖ፣ ሦስት የጥይት መጋዘኖችን ጨምሮ በአጠቃላይ 16 የተጠኑ ዒላማዎች ወድመዋል፡፡

በተዋጊ ጀቶች ደግሞ 108 የዩክሬን ወታደራዊ ኃይሎች እና የመሳሪያ አቅርቦቶች ይገኙባቸዋል ባለቻቸው አካባቢዎች ላይ ጥቃት ፈጽማለች፡፡

12 የዩክሬን ሰው አልባ የጦር ድሮኖች፣ ታንኮች፣ ሚሳዔሎች፣ እንዲሁም ዴፖዎችም በሩሲያ ሚሳዔሎች ተመተው መውደማቸውንም ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።

በመድፍ በፈጸመችው ጥቃት ደግሞ 315 የዩክሬን ወታደራዊ ዒላማዎች እንደተመቱና ሁለት ሚግ 29 ጀቶቻቸውም እንደወደሙ ነው የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር የገለጸው፡፡

የሩሲያ መንግስት ዩክሬን በመጪው የፋሲካ በዓል እና ከዛ በኋላ ባሉት ተከታታይ ቀናት ጥቃት ልትፈጽም እንደምትችል መረጃ እንዳለውና፥ ጥቃት የምትፈጽም ከሆነም ከሩሲያ በኩል በሚኖረው የአጸፋ ምላሽ ዕልቂት እንዳታስተናግድ ስጋት እንዳለው ማሳሰቡን ሬውተርስ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.