Fana: At a Speed of Life!

በአማራና አፋር ክልሎች ከ2 ሚሊየን በላይ ሰዎች ማኅበራዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) በአማራና አፋር ክልሎች አሸባሪው ህወሓት በፈጸመው ጥቃት ከ2 ሚሊየን 4 መቶ ሺህ በላይ ሰዎች ማኅበራዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የኢትዮጵያ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ገለጸ።

የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በአማራና አፋር ክልሎች ባደረገው የዳሰሳ ጥናት ግኝቶች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የተቋሙ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ዘውዱ ወንድም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ÷ የቁጥጥር ዳሰሳ ጥናቱ በክልሎቹ በጦርነቱ ምክንያት የተጎዱ ነዋሪዎችን መልሶ ለማቋቋም ከመንግሥት መቅረብ ባለባቸው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ላይ ያተኮረ እና የጉዳቱን ደረጃ ያመላከተ ነው ብለዋል።

የቁጥጥር ዳሰሳ ጥናቱ አራት ቡድኖችን በማዋቀር በአማራና አፋር ክልሎች 9 ዞኖች ላይ መካሄዱ ተመልክቷል፡፡

በተቋሙ የሴቶች፣ ሕጻናትና አረጋውያን ጉዳዮች ዳይሬክተር ወይዘሮ ቀለመወርቅ ታሪኩ ÷ በዳሰሳ ጥናቱ ከ1 ሚሊየን 855 ሺህ በላይ ሰዎች ማኅበራዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ለይተናል ብለዋል፡፡

ጥቃት በተፈጸመባቸው የአፋርና አማራ ክልሎች ዕድሜያቸው ከሥምንት ዓመት ሕጻን እስከ አዛውንት ባሉ 1ሺህ 217 ሰዎች ላይ ጾታዊ ጥቃት እንደተፈጸመና የሥነ ልቡና ጉዳት እንደደረሰባቸውም ጥናቱ አመላክቷል፡፡

ከሰብአዊ ጉዳት ባሻገር በሃይማኖት ተቋማት ፣ በግለሰብ ንብረቶች እንዲሁም በመንግሥትና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ላይ የንብረት ውድመት፣ ዘረፋና ቃጠሎ መፈጸሙም ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል በጦርነቱ ምክንያት ከአፋር ክልል በአጠቃላይ የተፈናቀሉ ከ645 ሺህ በላይ ዜጎች ናቸው ያሉት ደግሞ የተቋሙ የምርምር ዳይሬክተር አቶ አዳነ በላይ ናቸው።

6 ሺህ 609 ሰዎች አካላዊ ጥቃት፣ ከ145ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ የሥነ ልቦና ጉዳት እንደደረሰባቸውም የተገለጸ ሲሆን ትምህርት ቤቶች ፣የተለያዩ ተቋማት እና መኖሪያ ቤቶች በአስከፊ ሁኔታ መውደማቸውም በጥናቱ መጠቆሙን ኢዜአ ዘግቧል።

የሃይማኖት ተቋማት ያበረከቱት ማኅበራዊ ድጋፍ ከፍተኛ እንደነበር የተገለፀ ሲሆን በችግሩ ለተፈናቀሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚሰጠው ድጋፍ በቂ ባለመሆኑ በመጠኑ መሻሻል እንዳለበትም ተጠቁሟል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.