Fana: At a Speed of Life!

ዜጎች ለትንሳኤ እና ኢድ አልፈጥር ከሚፈጸም እርድ የሚገኝን ቆዳ በጥንቃቄ ለገበያ እንዲያቀርቡ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዜጎች በቀጣይ ከሚከበሩት የትንሳኤ እና የኢድ አልፈጥር በዓላት ከሚፈጸም እርድ የሚገኘውን ቆዳ በጥንቃቄ በማዘጋጀት ለገበያ እንዲያቀርቡ የቆዳ እና ቆዳ ውጤቶች ምርምርና ልማት ማዕከል ጥሪ አቅርቧል።
 
የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳኛቸው ሽፈራው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ በዓመት ከሚካሄዱ እርዶች ውስጥ በቀጣይ ከሚከበሩ የትንሳኤ እና የኢድ አልፈጥር በዓላት የሚፈጸመው እርድ 30 በመቶውን ይይዛል፡፡
 
ስለሆነም በዓላቱን ምክንያት በማድረግ በሚከናወን እርድ ወቅት ማህበረሰቡ ለቆዳ ጥራት ማለትም ቆዳው እንዳይቀደድ እና አጥንት እንዳይከሰከስበት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
 
ቆዳ በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋለ ትልቅ የሃገር ሃብት መሆኑን የገለጹት አቶ ዳኛቸው÷ ዜጎች ከእርድ በኋላ ቆዳውን በወቅቱ ለገበያ ማቅረብ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡
 
ከመጪዎቹ በዓላት ጋር ተይይዞ ከሚፈጸም እርድ የሚገኝን ቆዳ በአግባቡ ሰብስቦ ወደ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማድረሰ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ከክልል ቢሮዎች እና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጎ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱንም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
 
በዚህም ከእርድ የሚገኝን ቆዳ በጥንቃቄ ከማዘጋጀት ባለፈ በወቅቱ ወደ ገበያ በማውጣት እንዲሰበሰብ በአቅራቢዎች እና ተረካቢ ፋብሪካዎች መካከል የገበያ ትስስር መፈጥሩን ተናግረዋል፡፡
 
ቆዳ የሚሰበስብ አካል የለም ለሚለው ቅሬታ በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ወጣቶች ተደራጅተው ቆዳዎችን መሰብሰብ እንደሚችሉ ጠቁመው÷ በአንዳንድ አካባቢዎች የቆዳ መሰብሰቢያ ማዕከላት መኖራቸውን አንስተዋል፡፡
 
በዘርፉ ባለፉት 9 ወራት ከ22 ሚሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ መገኘቱን የገለጹት ዳይሬክተሩ÷በቀጣይ ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ እና የሥራ ዕድል ለማሳደግም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል፡፡
 
ማህበሰረቡ ቆዳ እና ሌጦ የአገር ሃብት መሆኑን በመገንዘብ ለቀጣዮቹ በዓላት ከሚፈጸም እርድ የሚገኝን ቆዳ ጥራቱን በጠበቀ መልኩ በማዘጋጀት በወቅቱ አቅራቢያ ለሚገኙ ገዥዎች ማስረከብ እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
 
በመላኩ ገድፍ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.