ቋሚ ኮሚቴው ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች ከመላ አገሪቱ መልምሎ ማሰልጠን እንደሚገባ አሳሰበ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማት፣ ስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች ከመላ አገሪቱ መልምሎ ማሰልጠን እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እየተገነባ ያለውን የቡራዩ ልዩ ተሰጥኦ ማዕከል ግንባታ ሂደትን ተመልክቷል።
በጉብኝቱም የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር ከይረዲን ተዘራ እንዳሉት÷በመላ አገሪቱ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች በመለየት በዘመናዊ የተግባር ትምህርት የታገዘ ስልጠና እንዲያገኙ ለማድረግ እየተገነባ ያለው ማዕከል ተማሪዎች የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተሰጥዖአቸው እንዲዳብርና የአገሪቱ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲፋጠን ያደርጋል ብለዋል።
የማዕከሉን የግንባታ ሂደት በአጭር ግዜ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲበቃ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበትና የተማሪዎች ልዩ ተሰጥዖን ከመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ጀምሮ ለማሳደግና ወደ ማዕከሉ ከመጡም በኋላ ብቁ ሆነው እንዲወጡ በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ከሚገኙ የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ቅንጅታዊ አሠራር ፈጥሮ መስራት እንደሚገባም አሳስቧል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር በለጠ ሞላ በበኩላቸው÷ የቡራዩ ልዩ ተሰጥዖኦማሰልጠኛ ማዕከል ከ800 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ከአምስት ዓመታት በፊት የግንባታ ስራው መጀሩን ገልጸዋል።
ግንባታውን በአጭር ግዜ አጠናቆ ከ2015 የትምህርት ዘመን ጀምሮ ከመላው ሀገሩቱ 1000 ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ርብርብ እየተደረገ ነው ማለታቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በወርቅአፈራው ያለው
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!