Fana: At a Speed of Life!

ቻይና በአስቸጋሪ ጊዜ ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም ላሳየችው አጋርነት የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ አክብሮትና ምስጋና አለው – አምባሳደር ተሾመ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ በቤጂንግ በሚገኘውና በቻይና ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ በሆነው ሴንተር ፎር ቻይና ኤንድ ግሎባላይዜሽን (Center for China and Globalization ) ተገኝተው ለተቋሙ መስራችና ፕሬዚዳንት ዶክተር ሁዪኦ ዋንግ እና በተቋሙ ለሚገኙ ምሁራን በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አምባሳደሩ በማብራሪያቸው በኢትዮጵያ የሰሜኑ ክፍል የተከሰተው ጦርነት መንግስት ተገዶ የገባበት መሆኑንና ከጅማሮው አንስቶ ጦርነቱን ለማስቀረት ከፍተኛና ተደጋጋሚ ጥረቶችን አድርጎ እንደነበር አስታውሰዋል።

ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላም መንግስት በጦርነቱ መሀል የተናጠል የተኩስ አቁም በማድረግ ለሰላም እድል ለመስጠት ከፍተኛ ስራ ሰርቷል ያሉት አምባሳደሩ በቅርቡም መንግስት ያልተገደበ የሰብዓዊ የተኩስ አቁም ውሳኔ በማሳለፍ የሰብዓዊ እርዳታ በየብስና በአየር እንዲደርስ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

አክለው ከየትኛውም የዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅት በላይ ከፍተኛውን የሰብዓዊ እርዳታ እያስተባበረና እየሰጠ የሚገኘው የኢትዮጵያ መንግስት መሆኑን ተናግረዋል።

ከምዕራቡ ዓለም በኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ስላለው ያልተገባ ጫና አምባሳደሩ ሲያብራሩ በተለይ አሜሪካና የአውሮፓ ህብረት የተለያዩ ማዕቀቦችን በኢትዮጵያ ላይ በመጣል ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን እያሳደሩ መሆናቸውንና ዓለም አቀፍ ሚዲያዎቻቸውን በመጠቀም በኢትዮጵያ ላይ ሰፊ የስም ማጥፋት ዘመቻ መክፈታቸውን አውስተዋል።

ነገር ግን በዚህ ሁሉ አስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ ቻይና ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም ላሳየችው ጠንካራ አጋርነትና እውነተኛ ወዳጅነት የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ አክብሮትና ምስጋና እንዳለው አስረድተዋል።

የተቋሙ መስራችና ፕሬዚዳንት ዶክተር ሁዪኦ ዋንግ በበኩላቸው÷ በሚዲያ ከሚሰሙት ይልቅ ከአምባሳደሩ በቀጥታ በአካል ስለኢትዮጵያ ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ለመስማትና ለመረዳት በመቻላቸው ያላቸውን ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይም ተቋማቸው ከኤምባሲው ጋር ያለውን ቅርብ ግንኙነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል መናገራቸውን በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.