Fana: At a Speed of Life!

በበዓል ወቅት የኃይል መቆራረጥን ለመፍታት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እንተከናወኑ ነው – የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የትንሳዔና የኢድ-አልፈጥር በዓላት መቃረባቸውን ተከትሎ ሊኖር የሚችለውን የኃይል መቆራረጥና መዋዥቅ ችግር ለመፍታት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በማከናወን ላይ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

ተቋሙ በበዓላቱ ዋዜማና ዕለት የኤሌክትሪክ ኃይል ሳይቆራረጥና ሳይዋዥቅ ለማቅረብ አስቀድሞ የቅድመ መከላከል ሥራዎች እየተሰራ ሲሆን፥ ችግሩ ከተከሰተ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የአስቸኳይ ጥገና ግብረ-ሃይል አዋቅሮ ወደ ስራ ገብቷል፡፡

መሰል ዝግጅቶች ቢደረጉም በተለይ በመጪው የትንሳኤ በዓል አሁንም መቆራረጥ ሊከሰት ስለሚችል ከሲሚንቶ ፋብሪካዎችና ወደ ውጭ ከሚልኩ ኢንዱስትሪዎች በስተቀር ሁሉም ኢንዱስትሪዎች በበዓሉ ዋዜማ ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ በዓሉ ዕለት ቀን 6 ሰዓት ድረስ ከዋናው የኃይል ቋት (ግሪድ) የሚያገኙትን የኤሌክትሪክ ኃይል ሙሉ ለሙሉ ባለመጠቀም የተለመደ ትብብራቸውን እንዲያደርጉ ተቋሙ ጠይቋል።

ደንበኞችም በቤት ውስጥ የሚገለገሉባቸውን የኤሌክትሪክ ቁሶች ኃይል ቆጣቢ እንዲሆኑ፤ ሲጠቀሙም ለአደጋ በማያጋልጥ መልኩ እንዲሆን ያስፈልጋል ነው ያለው አገልግሎቱ፡፡

እንዲሁም የኤሌክትሪክ ኃይል ጭነት በማይበዛበት ሰዓት በተለይም ከምሽቱ 4 ሰዓት እስከ ንጋቱ 11 ሰዓት ባለው ጊዜ ቢጠቀሙ የተሻለ የኤሌክትሪክ ኃይል ከማግኘት ባለፈ የኤሌክትሪክ መቆራረጥን ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ከአገልግሎቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል በሚቋረጥበት ጊዜ የጥገና ስራ ለማከናወን የተቋሙን መታወቂያ የያዙ የቴክኒክ ባለሙያዎች በተለያዩ አካባቢዎች ለስራ ጉዳይ እንደሚንቀሳቀሱ ህብረተሰቡ ተገንዝቦ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግና የተቋሙ የጥገና ሰራተኞች በመምሰል መሠረተ ልማቱ ላይ ስርቆትና ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ አካላት ሊኖሩ ስለሚችሉ ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስቧል፡፡

በተጨማሪም ደንበኞች ማንኛውንም መረጃዎች ለመጠየቅ፣ ጥቆማዎችና አስተያይቶች ለማቅረብ ወደ አቅራቢያቸው የሚገኝ የአገልግሎት መስጫ ማዕከል በአካል በመሄድ ወይም በ905 ነፃ የጥሪ ማዕከል ማሳወቅ ይችላሉ ብሏል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.