የሀገር ውስጥ ዜና

የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ለትንሳኤ በዓል ዝግጅት ማጠናቀቁን ገለፀ

By Alemayehu Geremew

April 20, 2022

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ለትንሳኤ በዓል ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገለፀ፡፡

በዓሉን ምክንያት በማድረግም 3 ሺህ የዳልጋ ከብት 5 ሺህ በግና ፍየል ለዕርድ ማዘጋጀቱን አስታውቋል።

ከኅብረተሰቡ የሚመጡ የእርድ እንስሳትንም ለማስተናገድ ማሽኖቹን ዝግጁ ማድረጉን ገልጿል፡፡

በዕለቱ የሰው ኃይል እጥረት እንዳይጋጥምም ድርጅቱ 200 ጊዜያዊ ሰራተኞ መቅጠሩን ነው ያስታወቀው።

በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበርና የኢትዮጵያ የቁም እንስሳት ነጋዴዎች ማኅበርም ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡

ከ30 እስከ 40 ሺህ የሚጠጉ የእርድ እንስሳትም ወደ ከተማዋ የግብይት ስፍራዎች እንዲገቡ መደረጋቸውም ነው የተመለከተው፡፡

በቤትና በተለያዩ አካባቢዎች የሚከናወኑ እርዶች ከእንስሳት ወደ ሰው ለሚተላለፉ በሽታዎች ተጋላጭ ስለሚያደርጉ፥ ህብረተሰቡ ወደ ቄራዎች ድርጅት በመምጣት እንዲጠቀምም ጥሪ ቀርቧል።

በድርጅቱ የመሸጫ ሱቆች በቂ አቅርቦት እንደሚኖር የተገለጸ ሲሆን፥ የበሬ ስጋ በኪሎ እስከ 350 ብር የፍየልና የበግ እስከ 260 ብር እንደሚሸጥም ተነግሯል።

ከተማ አስተዳደሩ በህገወጥ እርድ ምክንያት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ያጣል ተብሏል።

በዘቢብ ተክላይ