ዓለምአቀፋዊ ዜና

ሩሲያ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ልትጠቀም ትችላለች በሚል የቀረበባትን ክስ ውድቅ አደረገች

By Meseret Awoke

April 20, 2022

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት የኑክሌር ጦር መሳሪያ ልትጠቀም ትችላለች በሚል የቀረበባትን ክስ እንደማትቀበል የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቭሎዶሚር ዘነልስኪ ከቀናት በፊት ከቺኤን ኤን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ። ሩሲያ ታክቲካዊ የኑክሌር ጦር መሳሪያ የመጠቀም ሀሳብ እንዳላት ያመላከቱ ሲሆን፥ የሩሲያ ኑክሌር መሳሪያን የመጠቀም ሀሳብ ዩክሬንን ብቻ ሳይሆን አገራትንና ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ሊያሳስብ ይገባል ነበር ያሉት፡፡

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ኢንዲያ ቱ ዳይ ከተባለ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ለፕሬዚዳንት ዘነልስኪ ክስ በሰጡት ምላሽ “ሩሲያ በወታደራዊ ዘመቻው የኑክሌር ጦር መሳሪያ እጠቀማለሁ ብላ አታውቅምም፥ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ስለመጠቀም የተናገረ ሰው ካለ ዘለንስኪ (ፕሬዚዳንት) ብቻ ነው” በማለት አስተባብለዋል፡

አክለውም “ ዘነልስኪ በሚዘባርቀው ነገር ሁሉ መልስ መስጠት አይጠበቅብንም” ሲሉ ላቭሮቭ የዩክሬኑን ፕሬዚዳንት ንግግር አጣጥለውታል፡፡

“በኑክሌር ጦርነት ማንም አሸናፊ ሊሆን አይችልም” ሲሉ ደጋግመው የተናገሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላቭሮቭ፥ ሩሲያ በዩክሬን ወታደራዊ ዘመቻ ከኑክሌር ውጭ ያሉ መደበኛ የጦር መሳሪያዎች ላይ ትኩረቷን እንደምታደርግም ነው ያረጋገጡት።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝም የዩክሬን እና ሩሲያን የቃላት ምልልስ አስመለክተው ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት አስተያየት፥ በዚህ ወቅትየኑክሌር ግጭት የማይታሰብ ነው ማለታቸውን አር ቲ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!