Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የተቋማት ግንባታ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው -የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የክልሉን ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የተቋማት ግንባታ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የአማራ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ገለጸ፡፡

የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኋላፊ አቶ ግዛቸዉ ሙሉነህ የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ÷ በክልሉ ስራዎችን ለማከናወን ሰላም መሰረታዊ ነገር በመሆኑበ ክልሉም ለጉዳዩ ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ ነዉ ብለዋል።

ከጦርነቱ ወዲህ አብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች ሰላማዊና ለልማት የተመቹ ቢሆንም አሁንም ግን በተለያዩ ቦታዎች ለዜጎች ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆኑ ችግሮች እየተፈጠሩ ነዉ ብለዋል።

ሰሞኑን በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን እና በሰሜንሸዋ ዞን የተፈጠሩትን ግጭቶች የጠቀሱት ኃላፊዉ በአካባቢው የሚከሰተዉ ተደጋጋሚ ግጭት የኦሮሞና የአማራን ህዝብ ማጋጨት የሚሹ አካላት ከጀርባ ያሉበት ነዉ ብለዋል።

ይሁንና ከትናንት ጀምሮ አካባቢው ላይ የፀጥታሀይሎች መሰማራታቸዉና የዞን አመራሮች ፣ ሽምግልናን ጨምሮ በተሰሩ ስራዎች አካባቢዉ ወደመደበኛ ሰላሙ መመለሱን ተናግረዋል።

አካባቢዉ የሽብር ቡድኑ ሸኔ የሚንቀሳቀስበት እንደመሆኑ ለመሰል አለመረጋጋት የችግሩ ምንጭ ምንድን ነዉ በሚል ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሆነም ተናግረዋል።

በሌሎች አካባቢዎችም በተለይ በማዕከላዊ ጎንደር በፅንፈኛ የቅማንት ቡድን ተመሳሳይ አለመረጋጋትን ለመፍጠር በተለያየ ጊዜ መንቀሳቀሱን ያነሱት አቶ ግዛቸዉ ቡድኑ የአሸባሪዉ ህወሀት መሸሸጊያና መጠቀሚያ የመሆን እንቅስቃሴዎች መኖራቸዉንና ክልሉም ይህንኑ የመመከት ስራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ ለሚኖር ዘላቂ ሰላም ግን የክልሉን የፀጥታ ተቋማት ፣ የፖሊስ ፣ ልዩ ሀይል እና ሚሊሻ አባላትን የማሰልጠንና የማደራጀት ስራ እየተሰራ ነዉም ብለዋል ።

በኢኮኖሚ ዘርፍ ግብርናን ቀዳሚ ባደረገዉ ስራም ቀደም ሲል በችግር ዉስጥ ሆኖ በ2013/14 የምርት ዘመን 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት የታረሰ እና 118 ሚሊየን ኩንታል እህል ምርት የተገኘ ሲሆን ÷ ይህም የክልሉ ምርታማነት በሄክታር 26 ነጥብ 2 ኩንታል መሻሻል የታየበት መሆኑን ተናግረዋል።

በጸጋየ ወንድወሰን

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.