በአውሮፓ “ምንነቱ ያልታወቀ የጉበት በሽታ” እየተስፋፋ መሆኑ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአውሮፓ “ምንነቱ ያልታወቀ የጉበት በሽታ” (ሄፓታይተስ) ወረርሽኝ እየተስፋፋ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የአውሮፓ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል በሰጠው መግለጫ ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ በበሽታው በርካታ ህጻናት መያዛቸውን የተመለከተ ሪፖርት ደርሶኛል ብሏል፡፡
ብሪታንያ የዚህን በሽታ ሪፖርት ለማዕከሉ በማሳወቅ ቀዳሚዋ ስትሆን በቀናት ውስጥም በርካታ የታማሚዎች ቁጥር ማስመዝገቧን ማዕከሉ አስታውቋል፡፡
በእንግሊዝ የሚገኙ ታማሚዎችም በህመሙ ምክንያት የጉበት ኢንዛየማቸው መጠን መጨመሩ የተገለፀ ሲሆን የሆድ እና የጨጓራ ህመም ምልክቶችን ማሳየታቸው ተመላክቷል፡፡
ከዚህ ባለፈም ማስመለስና ማስቀመጥ በተወሰኑ ታማሚዎች ላይ ተስተውሏልም ነው ያለው ማዕከሉ፡፡
የብሪታኒያ የጤና ደህንነት ኤጀንሲ እንደገለፀው የህፃናት የጉበት በሽታ ከእንግሊዝ በተጨማሪ በዴንማርክ፣ አየርላንድ፣ ኔዘርላንድስ እና ስፔን መከሰቱን አስታውቋል፡፡
ወረርሽኙ በአሜሪካ አላባማ ግዛት የተከሰተ ሲሆን ከአንድ እስከ ስድስት ዓመት የዕድሜ ክልል የሚገኙ ዘጠኝ ሕፃናት ላይ ምልክቱ መታየቱን የአውሮፓ በሽታ መከላከያ መቆጣጠሪያ ማዕከል ገልጿል፡፡
የአጣዳፊ ሄፓታይተስ ወረርሽን የተከሰተበት ምክንያት እስካሁን ያልታወቀ ሲሆን የህክምና ባለሙያዎች የወረርሽኙን መንስኤ ለማወቅ የተለያዩ ምርመራዎችን በማድረግ ላይ መሆናቸውን ገልጿል፡፡
የብሪታኒያ የህክምና ቡድን በአንፃሩ ባክቴሪያ፣ ጥገኛ ህዋሳት እና ጀርም ወይም በአካባቢው ያሉ መርዛማ ነገሮች ለወረርሽኙ መከሰት ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ መላምቱን አስቀምጧል፡፡
በቫይረሱ የተያዙት ህጻናትም ከሚያሳዩት ምልክት አንጻር የሚያመሳስላቸው ነገር እምብዛም መሆኑንም አመላክቷል፡፡
የህክምና ቡድኑ አባላት ወረርሽኙ ከኮሮና ቫይረስ ክትባቶች ጋር ሊገናኝ የሚችልበት እድል ሊኖር እንደሚችልም መጥቀሳቸውን አር ቲ ዘግቧል፡፡
ይሁን እንጅ እስካሁን ከቫይረሱ ጋር ሊያዛምድ የሚችል ነገር አላገኘንም ያሉት የህክምና ቡድኑ አባላት፥ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የሰዎችን አመጋገብ ጨምሮ ልማድና መሰል ነገሮች ላይ ጥናት ማድረጋቸውንም ነው የገለጹት፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!