Fana: At a Speed of Life!

የሰብአዊ ድጋፍ የጫኑ 30 ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ ለመጓዝ ዝግጁ መሆናቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ምግብ ፕሮግራም የሰብአዊ ድጋፍ የጫኑ 30 ከባድ ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ ለመጓዝ ዝግጁ መሆናቸውን አስታወቀ።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ የኮሙኒኬሽን ኃላፊ ክሌር ኔቪል እንደገለጹት፥ ለአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ የሚያስፈልጉ አቅርቦቶችና አልሚ ምግቦችን የያዙ 30 ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ ለመጓዝ ዝግጁ ሆነዋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ መንግስትን የሰብአዊ ተኩስ አቁም ውሳኔ በበጎ ጎኑ ያየዋል ያሉት ኃላፊዋ፥ ተቋሙና አጋሮቹ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚያስፈልገውን ሰብአዊ ድጋፍ የማድረስ አቅም አላቸው ብለዋል።

እ.አ.አ 2022 የሚያዚያ ወር መጀመሪያ አንስቶ እርዳታ ጫኝ ተሽከርካሪዎች በአፋር በኩል ወደ ትግራይ ደህንነታቸው ተጠብቆ የመጓዝ ሁኔታ ላይ መሻሻል መታየቱንና ይሄን መልካም ጅማሬ በማሳደግ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ወገኖች በየቀኑ እርዳታ ማድረስ እንደሚያስፈልግ ነው የኮሙኒኬሽን ኃላፊዋ ያስረዱት።

በጦርነቱ ምክንያት በትግራይ፣ አፋርና አማራ ክልሎች የምግብ እርዳታ ከሚያስፈልጋቸው ውስጥ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ለ3 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በዚሁ መሰረት ተቋሙ በትግራይ ክልል 2 ነጥብ 13 ሚሊየን፣ በአማራ ክልል 650 ሺህ እና በአፋር ክልል 630 ሺህ ሰዎችን ለመደገፍ ማቀዱን ኃላፊዋ አብራርተዋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራምና አጋሮቹ በሰሜን ኢትዮጵያ በጦርነቱ ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች የሚያስፈልገውን የሰብአዊ ድጋፍ መጠን ተደራሽ ለማድረግ ዝግጁ ናቸው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከእ.አ.አ 2021 መግቢያ አንስቶ በአፋር፣ ትግራይና አማራ ክልሎች በጦርነቱ ምክንያት ለተጎዱ ከ4 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ወገኖች የሕይወት አድን የምግብ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.