Fana: At a Speed of Life!

በቀጣይ ቀናት ለሚከበሩት በዓላት የአቅርቦት ችግር እንዳይከሰት ዝግጅት ተደርጓል – የድሬዳዋ አስተዳደር

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀጣይ ቀናት በክርስትና እና እስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ለሚከበሩት ለትንሳኤና ለኢድ አልፈጥር በዓላት የአቅርቦት ችግር እንዳይከሰት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መሰራታቸውን የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀርቢ ቡህ÷ አስተዳደሩ አላስፈላጊ የሆነ የዋጋ ንረት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ጠቁመው÷ በተለይም ገበያውን ሊያረጋጉ የሚችሉ ስራዎችን ከመስራት አንስቶ አላስፈላጊ የዋጋ ንረት በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይም እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበቱ በተለይም የፍላጎትና የአቅርቦት አለመመጣጠን ፣ የገበያ ሰንሰለቱና አቅርቦት መዛባት ፣ አላግባብ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች ለችግሩ መከሰት መንስኤ መሆናቸውን ጠቁመው÷ ይህንኑ ችግር ለመፍታትም ግብረ ኃይል በማቋቋም ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል፡፡
የቅዳሜና እሁድ ገበያ የዋጋ ንረቱን በማረጋጋት ዓይነተኛ ሚና እንዳለው ገልጸው÷ በዚህም በገበያዎቹ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ምርቶችን በማቅረብ አምራቹንና ሸማቹን በማገናኘት አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሬን ማስቀረት መቻሉን ነው የተናገሩት፡፡
ለፋሲካ እና ኢድ አል ፈጥር በአላት የአቅርቦት ችግር እንዳይከሰት ተገቢው ዝግጅት መደረጉን ያረጋገጡት ምክትል ከንቲባው÷ ለአብነትም የዘይት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት በዘጠኙም ቀበሌዎች ዘይት ተከፋፍሏል ማለታቸውን ከድሬ ዳዋ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.