Fana: At a Speed of Life!

ዩኒቨርሲቲው የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲፈታ በምርምርና ጥናት ለማገዝ እየሰራ መሆኑን አሰታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በመንግስት መዋቅር ውስጥ ውስብስብ እየሆነ የመጣውን የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር እንዲፈታ በጥናትና ምርምር ለማገዝ እየሰራ መሆኑን የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው እያከናወነ ባለው የሪፎርምና የአቅም ግንባታ ስራዎቹ ዙሪያ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጠ ሲሆን÷ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ዶክተር ገረመው ሁሉቃ እንደገለጹት÷ በየደረጃው ባሉ የመንግስት ተቋማት የመልካም አስተዳደር እጦትና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር የህዝብ ብሶት የሚስተናገድባቸው ሆነዋል።

ችግሩ ውስብስብና የተለየ መፍትሔ የሚፈልግ መሆኑን ጠቅሰው÷ በተለይ በህዝባዊ ውይይት ጎልተው የወጡትን ችግሮች እንዲፈቱ በጥናትና ምርምር የመፍትሔ አማራጮች ላይ በመስራት እናግዛለን ነው ያሉት።

ዩኒቨርሲቲው በአመራሮች ዘንድ የሚታየውን የመፈፀምና የማስፈፀም አቅም ውስንነት ችግር ለማቃለል የአቅም ግንባታ ስልጠና “ማኑዋል” እያዘጋጀ መሆኑንም ዶክተር ገረመው ተናግረዋል።

በአቅም ግንባታ፣ በተቋማዊ ሪፎርም፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በማማከር ስራዎች ከክልሉ እና ከፌዴራል ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራን ነውም ብለዋል።

አዲስ ስትራቴጂ፣ የስርዓተ ትምህርትና ስልጠና “ማኑዋሎችን” እና ” ሞጁሎችን” በሰለጠነ የሰው ሃይል የማደራጀት ስራ እየተሰራ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከደቡብ ኮሪያ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ኩባ፣ ከናዳና ኬንያ ካሉ አቻ ተቋማት ጋር በአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ፣ በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና መልካም አስተዳደር ውስጥ እያጋጠሙ ያሉትን ችግሮችን በጥናትና ምርምር ለመፍታት ልምድ ለመለዋወጥ በትብብር እየሰራን ነው ብለዋል ዶክተር ገረመው።

በተጨማሪም አቻ ተቋማቱ የደንበል ሃይቅ የእንቦጭ አረም ለማስወገድ በሚሰሩ ተግባራት ላይም እየተባበሯቸው መሆኑን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያና በሁለተኛ ድግሪ ከ50 በላይ በሆኑ ፕሮግራሞች ተማሪዎችን ተቀብሎ እያሰለጠነ እንደሚገኝ ያወሱት ዶክተር ገረመው÷ በፌዴራሊዝምና ፖሊሲ ጥናት ደግሞ የሶስተኛ ዲግሪን ለማስጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.