Fana: At a Speed of Life!

የሻሸመኔ ነዋሪዎች አሸባሪውን ሸኔ በፅናት ታግለን እኩይ ዓላማውን እናመክናለን አሉ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከመንግሥት ጎን ተሰልፈው አሸባሪው ሸኔን በፅናት በመታገል እኩይ ዓላማውን እንደሚያመክኑ የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

አሸባሪው ሸኔ ንጹሃንን በመግደል፣ ሀብት ንብረት በመዝረፍና በማውደም እኩይ ተግባር እየፈጸመ እንደሆነ ተናግረዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት፥ ሸኔ በተባለው አሸባሪ ቡድን የሚፈጸም ግድያ እና ማፈናቀል እንዳንገሸገሻቸው ነው የተናገሩት።

ቡድኑ የሕዝብ ስጋት እንዳይሆን ለማድረግ በሚካሄደው ሁሉን አቀፍ ትግል ከክልሉ መንግስት ጎን ሆነው የድርሻቸውን እንደሚወጡም ነዋሪዎቹ አረጋግጠዋል።

መንግሥት በሽብር ቡድኑ ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ ትክክልና የሚደገፍ እንደሆነ ገልጸው፥ የጥፋት ቡድኑን መግቢያና መውጫ ተከታትለው ለፀጥታ አካላት ትክክለኛ መረጃ በመስጠት የዜግነት ግዴታቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።

አሸባሪው ሸኔን ለማጥፋት እየተደረገ ላለው ጥረት የሕዝቡ ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፥ በምዕራብ አርሲ ዞን ሄባን አርሲ ወረዳ ሲንቀሳቀስ የነበረውን የአሸባሪው ሸኔ ቡድን የአካባቢው ህዝብ ከመንግሥት የፀጥታ አካላት ጎን ተሰልፎ ማጥፋት መቻሉን ለአብነት አንስተዋል።

የሄባን አርሲ ወረዳን ሕዝብ ተሞክሮ በማስፋት በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች የሚሽሎከለከውን የሽብር ቡድን ማስወገድ እንደሚገባም አሳስበዋል።

አሸባሪው ሸኔ የኦሮሞን ባህል፣ ወግና ሥርዓት የማያከብርና የማይወክል የሽብርተኞች ስብስብ ቡድን በመሆኑ በጋራ ትግል እንዲጠፋ ለማድረግ ትግላቸውን አጠናከረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.