Fana: At a Speed of Life!

የማረሚያ ተቋማት የሰብዓዊ መብት አያያዝ መሻሻሉን ቋሚ ኮሚቴው አረጋገጠ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቃሊቲ እና የቂሊንጦ ማረሚያ ቤቶች የሰብዓዊ መብት አያያዝ እና አጠባበቅ መሻሻሉን የሕግ፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ዛሬ ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የሥራ ኃላፊዎች እና ከተጠቀሱት ማረሚያ ቤቶች ኃላፊዎች ጋር በታራሚዎች የሰብዓዊ መብት አያያዝ እና አጠባበቅ ረገድ ውይይት አካሂዷል፡፡

በወቅቱም ከዚህ በፊት በሁለቱ ማረሚያ ቤቶች ሰፊ ቅሬታ ሲያስነሳ የነበረው የሰብዓዊ መብት አያያዝ እና አጠባበቅ መሆኑን ኮሚቴው አስታውሶ፥ አሁን ላይ በዘትፉ መሻሻል መኖሩን በመስክ ምልከታ ማረጋገጡን ገልጿል፡፡

ከጤና አገልግሎት፣ ከጥበቃ እና ከአባላት ስነ-ምግባር እንዲሁም ከአመክሮ ሂደት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ክፍተቶችን ለመሙላት ደግሞ በትኩረት መሥራት እንዳለበት አሳስቧል፡፡

ማረሚያ ቤቶቹ ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ ሕጻናትን እና ነፍሰ-ጡር እናቶችን፣ ዓቅመ-ደካሞችን እና አረጋውያንን በከፍተኛ የኃላፊነት መንፈስ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ቋሚ ኮሚቴው አመላክቷል፡፡

በተጨማሪም በማረሚያ ቤት ውስጥ ለትምህርት የደረሱ ዜጎች እስከ ኮሌጆች እና ዩኒቨርስቲዎች ድረስ እንዲማሩ የተፈጠረላቸው የትምህርት ዕድል ይበል የሚያሰኝ ነው ብሏል ኮሚቴው፡፡

የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽነር አቶ ዳመነ ዳሮታ በበኩላቸው ፥ ማረሚያ ቤቶች በአዋጅ የተሰጣቸው ስልጣን እና ኃላፊነት ሴክተር-ዘለል የሆኑ ሰፋፊ ሥራዎችን የሚሠሩ ዜጎችን አርሞ እና ቀርጾ ማውጣት ነው ብለዋል፡፡

ሆኖም ከዚህ በተቃራኒው በብዙዎች ዘንድ የጨለማ ቤት ብቻ ተደርጎ የሚታይበት ሁኔታ ሊቀረፍ እንደሚገባ ያሳሰቡት ኮሚሽነሩ ፥ ለብዙዎች ሰፊ የሥራ ዕድልም እየፈጠረ በመሆኑን የገጽታ ግንባታ በሰፊው እየተሠራ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ዋና ዳይሬክተር ኮማንደር ጫላ ፀጋ ፥ የማረሚያ ተቋሙ ከሆስፒታሎች ጋር ያለው የሥራ ግንኙነት በመቋረጡ፣ በሪፌራል የሚላኩ የማረሚያ ቤቱ ታካሚዎች በገንዘብ እየታከሙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በምልከታው ወቅት ‘የተቋሙ የጤና ተቋም የመድኃኒት አቅርቦት ውስንነት መኖሩን ታዝቤያለሁ’ ማለቱ ትክክለኛ ዕይታ ነው ብለዋል፡፡

የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ምክትል ኮሚሽነር ኮማንደር ሙላት ዓለሙ፥ በቋሚ ኮሚቴው ምልከታ ወቅት ‘የፍርድ ውሳኔ ሳያገኙ እና ፍርድ ሳይሰጡ የሚቆዩት ግለሰቦች መኖራቸውን አረጋግጫለሁ’ ማለቱ ትክክል መሆኑን አምነው፤ የፍርድ ውሳኔ ያላገኙትን ግን በቀነ ቀጠሮ በተገቢው መንገድ የማቅረብ ሥራ እየተሠራ እንደሆነ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ምክትል ኮሚሽነሩ በታራሚዎች የሚነሳውን የይቅርታ ጥያቄ ቅሬታን በተመለከተ ፥ ጉዳዩ በቀጥታ ተቋሙን እንደማይመለከት እና ማረሚያ ቤቱ ከፍርድ ቤቶች በሚሰጠው መስፈርት መሠረት ታራሚዎችን የመመልመል ሥራ ብቻ እንደሚያከናውን አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ የተመለመለ ሁሉ ይቅርታ ይደረግለታል ማለት እንዳልሆነም መግለጻቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በምልከታው ወቅት ከታራሚዎች፣ ከማረሚያ ቤቶች የጥበቃ አባላት እና ማኅበረሰቡ ጋር ውይይት ያደረገ ሲሆን ፥ በወቅቱ በክፍተትነት የተነሱ ጉዳዮችን ማረሚያ ቤቶች በተገቢው መልኩ ማየት እና የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት በትኩረት መሥራት እንዳለባቸው አሳስቧል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.