Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ ለበዓላት የቀረቡ መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ስርጭትን እየተቆጣጠረ መሆኑን አስተዳደሩ ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለቀጣዮቹ የትንሳኤ እና የኢድ አልፈጥር በዓላት ለገበያ የቀረቡ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች በተገቢው ሁኔታ እንዲሰራጩ አስፈላጊው ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህብረት ስራ ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡
 
በኤጀንሲው የግብይትና መሰረተ ልማት ዳይሬክተር ወ/ሮ ደብሪቱ ለአለም ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ በቀጣይ የሚከበሩትን የትንሳኤ እና የኢድ አልፈጥር በዓላትን ታሳቢ በማድረግ ለበዓላቱ የሚያስፈልጉ የፍጆታ ምርቶች በሸማች ህብረት ስራ ማህበራት በኩል ቀርበዋል፡፡
 
የምርት አቅርቦት እጥረት እና ስርጭት ችግር እንዳይፈጠርም ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ፣ ከገበሬዎች አምራች ህብረት ስራ ማህበራት፣ ከኢንዱስትሪ ግብዓት አምራች ፋብሪካዎች እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
 
ለበዓላቱም 120 ሺህ ኩንታል ስኳር፣ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ሊትር ዘይት፣ 41 ሺህ ኩንታል የስንዴ ዱቄት 1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ እንቁላል እና ከ50 ሺህ ኩንታል በላይ ሽንኩርት በከተማዋ በሚገኙ የህብረት ስራ ማህበራት በኩል መቅረባቸውን ነው የገለጹት፡፡
 
በሌላ በኩል በ11ዱም ክፍለ ከተሞች በሁሉም ወረዳዎች በሚገኙ የሸማች ህብረት ስራ ማህበራት በተዘጋጁ ኤግዚብሽን እና ባዛር አማካይነት ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ምርቶች መቅረባቸውንም ጠቁመዋል ፡፡
 
በመደበኛ ነጋዴዎች በኩል ለበዓሉ ከ30 እስከ 40 ሺህ የቁም እንሰሳት መቅረባቸውን የገለጹት ዳይሬክተሯ፥ ከዚሁ ውስጥ 2 ሺህ 200 የቁም ከብቶች በሸማች ህብረት ስራ ማህበራት በኩል መቅረባቸውን አንስተዋል፡፡
 
የስርጭትና የአቅርቦት ስራዎች በተገቢው መልኩ እንዲከናወኑም እስከ ታችኛው የገበያ ሰንሰለት ድረስ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ አስፈላጊው ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
 
ማህበረሰቡም በግብይት ስርዓቱ በነጋዴዎችም ሆነ በሌሎች አካላት ገበያውን የሚያውክ ድርጊት ተፈፅሞ ሲመለከት በአቅራቢያ ለሚገኙ የጸጥታ አካላት እንዲጠቁም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
 
በመላኩ ገድፍ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.