Fana: At a Speed of Life!

የባለቤቱን ፊርማ አስመስለው በመፈረም ከ12 ሚሊየን ብር በላይ ወጪና ገቢ ያደረጉ ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሂሳብ ባለቤቱ ቼክ ፈርሞ ባልሰጠበት ሁኔታ የባለቤቱን ፊርማ አስመስለው በመፈረም ከ12 ሚሊየን ብር በላይ ወጪና ገቢ በማድረግ ከባድ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል የተባሉ ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ።

ግለሰቦቹ መንግስታዊ ሰነዶችን በሀሰት አስመስሎ በማዘጋጀትና በሀሰተኛ ሰነድ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው  ነው በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች  ዳይሬክቶሬት ጄነራል  ዐቃቤ ህግ ክስ የመሰረተባቸው።

የዐቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያስረዳው÷ተከሳሽ  ሹክረዲን ሙሃመድ እና ሳሙዔል ዳምጤ እንዲሱም  መሳይ ታደሰ ጥር 21 ቀን 2014 ዓ.ም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዋሽ 7 ቅርንጫፍ ደንበኛ በሆኑት መዲና ሔንኬብ የውሃ ስራዎች ድርጅት ከተንቀሳቃሽ ሂሳብ ቁጥራቸው ላይ የሂሳቡ ባለቤት ቼክ ፈርመው ባልሰጡበት ሁኔታ የሂሳብ ባለቤቱን ፊርማ አስመስለው በመፈረም እረስ በርሳቸውና በሌሎች ግለሰቦች 12 ሚሊየን 235 ሺህ ብር  ወጪና ገቢ ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም ሀሰተኛ ቼኮችን በማቅረብ የወሰዱትን ገንዘብ ለመደበቅና ከህግ ተጠያቂነት ለማምለጥ በማሰብ የሞባይል ባንኪንግን ተጠቅመው በተለያዩ ግለሰቦች ወደተከፈተ አካውንት ያስተላለፉ በመሆኑ ተከሳሾች ፈጽመዋል በተባለው መንግስታዊ ሰነዶችን በሀሰት አስመስሎ ማዘጋጀትና በሀሰት ሰነድ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል አንዲሁም በወንጀል ድርጊት የተገኘን ሀብት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ተከሰዋል ተብሏል።

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ  የሙስና ወንጀል ቸሎት በህግ ጥላ ስር ላለው 1ኛ ተከሳሽ የክስ ቻርጁ እንዲደርሰው ተደርጎ የክስ መቃወሚያ ካለው እንዲያቀርብ እንዲሁም ያልተያዙትን  2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ደግሞ÷ ፖሊስ አፈላልጎ እንዲያቀርብ በማዘዝ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል መባሉን ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.