lung cancer concept. doctor explaining results of lung check up from x-ray scan chest on digital tablet screen to patien

ጤና

ቻይና የሳንባ ካንሰርን ማዳን የሚያስችል ትልቅ ግኝት ይፋ አደረገች

By Alemayehu Geremew

April 21, 2022

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቻይና እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በገዳይነቱ የሚታወቀውን የሳንባ ካንሰር በቀላል ቀዶ ጥገና ማከም እና ማዳን የሚቻልበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን በቻይና ቤጂንግ የሚገኝ የሕክምና ምርምር ማዕከል አስታወቀ፡፡

በቻይና ቤጂንግ የሕክምና ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገኝ የሳንባ ካንሰር ምርመራ እና ሕክምና ምዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ዢ ዡዪ እንደተናገሩት ÷ ለኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሲካሄዱ የቆዩ የሳንባ ምርመራዎች ለሳንባ ካንሰር መነሻ የሆኑ ምክንያቶችን እንድንለይ አስችሎናል ብለዋል፡፡

የሳንባ ካንሰርን በጊዜ መለየት ከተቻለና ሕክምና ከተደረገ የመዳን ዕድሉን በእጅጉ ማፍጠን እንደሚቻል ተመልክቷል፡፡

የሳንባ ካንሰር ሕሙማኑ እንደ ቀድሞው ቀዶ ጥገና ሳያስፈልጋቸው በደረት አካባቢ አነስተኛ ክፍተት በመፍጠር ቀጭን ቱቦ ላይ በተገጠመ ካሜራ እና ብርሃን ተመርቶ በሚሰራ አነስተኛ ቀዶ ጥገና እንደሚድኑም ነው ሲጂቲ ኤን የዘገበው፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት በፈረንጆቹ 2020 ባወጣው ሪፖርት መሰረት የሳንባ ካንሰር በገዳይነቱ ከጡት ካንሰር ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠ ሕመም ነው፡፡

በቻይና የሳንባ ካንሰር በገዳይነቱ በቀዳሚነት የሚቀመጥ ሲሆን በየዓመቱ 820 ሺህ አዳዲስ ሰዎች በሕመሙ ይጠቃሉ ፤ 710 ሺህ ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን ያጣሉ፡፡