Fana: At a Speed of Life!

ፀሎተ ሐሙስ በተለያዩ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓቶች ታስቦ ዋለ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 13 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፀሎተ ሐሙስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አብያተ ክርስቲያናት እና ገዳማት እንዲሁም በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ ሀይማኖታዊ ስነ ስርአቶች ታስቦ ውሏል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በመላ ሃገሪቱ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስነ ስርአቶች እየታሰበ ይገኛል።
በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ቤተክርስቲያን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስን ጨምሮ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናት እና ምዕመናን ተገኝተዋል።
ዕለቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ዝቅ ብሎ የሐዋርያቱን እግር በማጠብ ትህትናን ያስተማረበት ዕለት ነው። በዚህም አብነት የህጽበተ-እግር ሥነ-ሥርዓትን ታላላቅ አባቶች የምዕመናን እግር በማጠብ አከናውነዋል።
በተመሳሳይ ዕለቱ በባሕርዳር ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን፥ የፀሎተ ሐሙስ በዓልን የኢየሱስ ክርስቶስን ትህትናና ታዛዥነትን በሚያስተምሩ ሥነ-ሥርዓቶች ከምዕመናኑ ጋር እያሰበ ይገኛል።
በባሕርዳር ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ቤተክርስቲያን÷ እየተካሄደ ባለው በዚሁ መርሃ- ግብር ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አባልና በባሕርዳር እና አካባቢው ሀገረስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃምን ጨምሮ ቆሞሳት፣ ካህናት እና ዲያቆናት ተገኝተዋል።
ብፁዕነታቸው የቆሞሳቱ እና ካህናቱን፤ ካህናቱም የዲያቆናቱን እግር በማጠብ የኢየሱስ ክርስቶስን አርአያነት ተከትለው ሥርዓቱን ፈጽመዋል።
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ልደታ ማርያም የእምነቱ ተከታዮችና ምዕመናን የኢየሱስ ክርስቶስን ትህትናና ታዛዥነትን በሚያስተምሩ ሥነ ሥርዓቶች አስበዋል።
በፀጋዬ ወንድወሰን
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.