Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት 9 ወራት ከዳያስፖራው ከ1 ነጥብ 37 ቢሊየን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከዳያስፖራው ከ1 ነጥብ 37 ቢሊየን ብር በላይ ድጋፍ በገንዘብና በአይነት መሰብሰብ መቻሉን የኢትየጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡
 
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ከዳያስፖራ ማህበረሰብ ልማትና ተሳትፎ ጋር በተያያዘ የተከናወኑ ዋና ዋና ስራዎችን ገምግሞ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።
 
በግምገማውም የዳያስፖራውን ተሳትፎ የሚያጠናክሩ 876 የበይነ መረብና የገጽ ለገጽ ውይይቶ መካሄዳቸው፣ለዳያስፖራዎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱ፣የዳያስፖራ አባላት የውጭ ምንዛሬ አካውንቶች መከፈታቸው የዳያስፖራውን ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ እንዲጨምር ለማድረግ አስተዋፅኦ ማድረጋቸው ተመላክቷል፡፡
 
ዳያስፖራው ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ፣ለህልውና ዘመቻው፣በተለያዩ አካባቢዎች ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍና ለተጎዱ መሰረተ ልማቶች ግንባታ እና ለበጎ አድራጎት ስራዎች በአጠቃላይ 1 ነጥብ 37 ቢሊየን ብር ገቢ ማድረጉ ተገልጿል፡፡
 
ከዳያስፖራ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራዎች አኳያም 200 የሚሆኑ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻዎች በዳያስፖራው ተሳትፎ መካሄዳቸው፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ዳያስፖራው በሚኖርባቸው አገራት ያሉ ተመራጮች የኢትዮጵያን ዕውነታ እንዲረዱ ቅስቀሳዎች መከናወናቸውም በግምገማው ተጠቁሟል፡፡
 
በተለይም የበቃ ንቅናቄን እና ኤች አር 6600 እንዲሁም ኤስ 3199 ረቂቅ ህጎችን በመቃወም ሰልፎች በተለያዩ ከተሞች የተደረጉ ሲሆን÷ ከምክር ቤቶቹ ተመራጮች ጋር ውይይቶችና የተቃውሞ ፊርማ የማሰባሰብ ስራዎች በመካሄድ ላይ መሆናቸውም ተመላክቷል።
 
ታላቁ ጉዞ ወደ ሀገር ቤት ጥሪን ተከትሎም ዳያስፖራው ባደረገው የላቀ ተሳትፎ ዲፕሎማሲያዊ፣ ማህበረ-ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትሩፋቶች መገኘታቸው ተገምግሟል።
 
በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ የአገልግሎቱ ሃላፊ ዶ/ር መሐመድ እንድሪስ ባስተላለፉት መልዕክት÷ በቀሪ ጊዜያት ከታላቁ ጉዞ ወደ ሀገር ቤት የመጀመሪያ ጥሪ ስኬት መልካም ተሞክሮዎችን በመቅሰም በሁለተኛው ከኢድ እስከ ኢድ ወደ ሀገር ቤት ጉዞን ውጤታማ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
 
አመራሩ ከዚህም በተጨማሪ ተቋሙ የሚያስተባብራቸው ታላላቅ ሁነቶችን መሰነድ እንዲሁም የውስጥ አሰራርን ማሻሻል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ አቅጣጫዎችን መቀመጣቸውን ከዳያስፖራ ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.