የሀገር ውስጥ ዜና

7 ኩንታል የሚጠጋ በቆሎ ምርጥ ዘር በማስመሰል በህገ ወጥ መንገድ ሊሸጥ የነበረ ግለሰብ ተያዘ

By Alemayehu Geremew

April 21, 2022

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በስልጤ ዞን ጦራ ከተማ ቀለም በመቀባት ምርጥ ዘር አስመስሎ ሰባት ኩንታል የሚጠጋ በቆሎ በህገ ወጥ መንገድ ለሽያጭ ሲያዘጋጅ የነበረ ግለሰብ መያዙን ፖሊስ አስታወቀ።

የጦራ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ አዛዥ ሳጅን ረዲ ደኑር እንደገለጹት ÷ በቆሎ ቀለም በመቀባት ምርጥ ዘር በማስመሰል የሚያሰራጩ ግለሰቦች መኖራቸውን ከማህበረሰቡ በደረሳቸው ጥቆማ መሰረት ከአስተዳደሩ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ጋር በመቀናጀት ክትትል ሲያደርጉ ቆይተዋል።

በተደረገው ክትትል ዛሬ በከተማው ሚሊኒየም ቀበሌ በተለምዶ ቴሌ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሸቀጣ ሸቀጥ መደብር በተካሄደ ፍተሻ እንደተደረሰበት ተናግረዋል።

በዚህም ቀለም በመቀባት ምርጥ ዘር አስመስሎ በህገ ወጥ መንገድ የተዘጋጀ 7 ኩንታል የሚጠጋ በቆሎ ማግኘታቸውን የገለጹት ሳጅን ረዲ፥ ይህንኑ ለሽያጭ ሲያሰናዳ የነበረው ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉን አስታውቀዋል።

ግለሰቡ ለግል ጥቅሙ በማጭበርበር ኑሮውን ለማሸነፍ የሚታትረውን አርሶ አደሩን ኢኮኖሚውን የማዳከም ስራ ላይ በመሰማራቱ በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ምርመራ መጀመሩን ገልጸዋል።

ኅብረተሰቡ አካባቢውን በመቃኘት ህገ ወጦችን በማጋለጥ ያደረገውን ተነሳሽነት አጠናክሮ እንዲቀጥልም ሳጅን ረዲ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።