Fana: At a Speed of Life!

ለትግራይ ክልል የህክምና ቁሳቁስ የሚያቀርቡ አካላት የሚያቀርቡት ቁሳቁስ ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ማረጋገጥ አለባቸው – ኮሚሽኑ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 15 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለትግራይ ክልል የህክምና ቁሳቁስ እያቀረቡ ያሉ አጋሮች የሚያቀርቡት ቁሳቁስ ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ማረጋገጥ እንዳለባቸው የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ገለጹ።

አጋሮቹ በተለይም በጤና ዘርፍ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት መድሃኒት፣ የህክምና ቁሳቁስና አልሚ ምግብ በአየርና በየብስ ትራንስፖርት ተደራሽ እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል።

በተለይም ካለፈው ጥር ወር ጀምሮ ከአዲስ አበባ ወደ መቐለ በተደረገ 44 ያህል በረራ ለህክምና የሚያስፈልጉ ቁሳቁስና አልሚ ምግቦችን ማድረስ መቻሉን አንስተዋል።

የመድሃኒትና የህክምና አቅርቦት እጥረት በትግራይ ክልል ብቻ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያ የሚያጋጥም ክስተት እንደሆነ ጠቅሰው፥ የትግራይን ጉዳይ ፖለቲካዊ ማድረግ የሚፈልጉ አካላት ችግሩን የትግራይ ክልል ብቻ አድርገው ማንጸባረቃቸው ስህተት እንደሆነ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ለትግራይ ክልል የህክምና ቁሳቁስን ጨምሮ ሌሎች የሰብዓዊ ድጋፎችን ተደራሽ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ እንደሆነ አስታውሰው፥ ከአጋር አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የህክምና ቁሳቁስንና አልሚ ምግብ ተደራሽነትን ለማሳደግ በሳምንት ሁለት ጊዜ የነበረውን የአዲስ አበባ መቐለ በረራ ላይ ማሻሻያ መደረጉን አስታውሰዋል።

ወደ ክልሉ እየተጓዘ ያለው የህክምና ቁሳቁስና አልሚ ምግብ ለጤና ተቋማት በተለይም ለሆስፒታሎች በቂ እንደሆነ የገለጹት አቶ ምትኩ፥ እንደ ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ያሉ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ሃይሎች የሚያሰራጩት መረጃ መሰረት የሌለው እንደሆነ ገልጸዋል።

“እጥረት አጋጥሟል ከተባለ ከጀርባ የሚፈጸም አንድ የሆነ ሌላ ጉዳይ ሊኖር ይችላል” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.