Fana: At a Speed of Life!

በጋምቤላ ክልል የውስጥና የድንበር ዘለል የጸጥታ ችግሮችን ለመከላከል ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል-አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል የውስጥና የድንበር ዘለል የጸጥታ ችግሮችን ለመከላከል ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አሳሰቡ።
 
የክልሉ መንግስት የፀጥታ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባውን በጋምቤላ ከተማ አካሂዷል።
 
ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኡሞድ ኡጁሉ እንዳሉት÷ በክልሉ የውስጥና የድንበር ዘለል የጸጥታ ችግሮችን ለመከላከል ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
 
የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ከደቡብ ሱዳን ጋር በሚዋሰነው የጋምቤላ ክልል ውስጥ በመግባት በነዋሪዎች ላይ ከሚፈጸሙት ጥቃት በተጨማሪ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የቀንድ ከብቶች በተደጋጋሚ ዘርፈው ሲወስዱ እንደነበር አስታውሰዋል።
 
የጥፋት ሃይሎች በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ሊያደርሱ የሚችሉትን ጥፋት ለመከላከል መንግስት በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
 
ራሱን የጋምቤላ ነፃነት ግንባር/ጋነግ/ ብሎ የሚጠራው የአሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ተላላኪ እኩይ ሴራውን ለማምከን በትኩረት እየተሰራ እንደሆነ ነው የገለጹት።
 
ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ጨምሮ በክልሉ ጠረፋማ አካባቢዎች የደቡብ ሱዳን የሙርሌ ጎሳ አባላት የሚፈጽመውን ወንጀሎች በመከላከል ረገድ ከጸጥታ አካላቱ ከፍተኛ ኃላፊነት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
 
በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈንና ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ለማግታት ለሚደረገው ጥረት ስኬታማነት ማህበረሰቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር አቶ ኡሞድ ጥሪ አቅረበዋል።
 
በስብሰባው የክልሉና የአካባቢው የፀጥታ ሁኔታ የተገመገመ ሲሆን÷ ከውስጥ የፀጥታ ሁኔታ የከተማው የሌብነት፣ ስርቆትና ተራ ወንጀሎች ዙሪያ ሰፊ ውይይት ተደርጎል።
 
በተጨማሪም የኦነግ ሸኔ እናራሱን የጋምቤላ ነፃነት ግንባር (ጋነግ) ብሎ የሚጠራው ድርጅት እንቅስቃሴን በተመለከተ ውይይት ተካሂዷል።
 
የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ጥቃትና እንቅስቃሴ በድንበር አካባቢ የደቡብ ሱዳን አማፂያን ኃይሎች እያደረሱ ያለውን ጥቃት በተመለከተ ውይይት በማካሄድ አቅጣጫ መቀመጡን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.