Fana: At a Speed of Life!

የወባ በሽታ ቁጥጥር ስራዎችን ለማጠናከር 20 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ አጎበር ለማሰራጨት ታቅዷል – ጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በመጪው ክረምት የወባ ትንኝ ቁጥጥር ስራዎችን ለማጠናከር 20 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ አጎበር እንዲሁም 1 ነጥብ 6 ሚሊየን ቤቶችን ለመርጨት መታቀዱን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የጤና ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በዛሬው ዕለት የሚከበረውን የዓለም ወባ ቀን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም የወባ በሽታ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሐራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ ሀገራት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ዕድሜም ሆነ ፆታ ሳይለይ የሚያጠቃ ዋነኛ የጤና እና የማህበራዊ ዕድገት ችግር መሆኑን አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መልከዓ ምድር 75 በመቶ የሚሆነው ለወባ በሽታ ስርጭት አመቺ ነው ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው ÷ በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖረው 52 በመቶ ህዝብም ለበሽታው ተጋላጭ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በሽታው በአብዛኛው የሚከሰተው ዋናውን የክረምት ዝናብ ተከትሎ በመኸር ወይም በምርት መሰብሰቢያ ወቅት በመሆኑ አስቀድሞ በሽታውን መከላከል ዝግጅት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በዚህ መሰረት በቀጣዩ ክረምት የወባ ትንኝ ቁጥጥር ስራዎችን ለማጠናከር 20 ነጥብ 6 ሚሊየን አጎበር እንዲሁም 1 ነጥብ 6 ሚሊያን ቤቶችን ለመርጨት የሚያስችል 55 ሺህ 924 ኪሎ ግራም የቤት ውስጥ የፀረ-ወባ ትንኝ ርጭት ኬሚካል ገዝቶ ለማሰራጨት ዕቅድ መያዙን አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪም የወባ ምርመራና ህክምናን በተመለከተ 5 ነጥብ 5 ሚሊየን ህሙማንን ለመመርመር የሚያስችል ፈጣን የወባ መመርመሪያ ኪት እንዲሁም 4 ሚሊየን ህሙማንን ማከም የሚያስችል የፀረ-ወባ መድሃኒት ግዥና ስርጭት እየተካሄደ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

በልማት ኮሪደሮች የወባ በሽታ ምርመራና ህክምና አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ የልማት ቀጠና ባላቸው የተመረጡ አካባቢዎች ላይ 226 ጊዜያዊ የአገልግሎት መስጫ ጣቢያዎችን መቋቋማቸውን ጠቁመዋል።

የፊታችን ሚያዚያ 21 ቀን2014 ዓ.ም ህብረተሰቡንና የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት በማህበረሰብ ንቅናቄ በማሳተፍ በአዳማ ከተማ የወባ ቀንን በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ለማክበር የቅድመ ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.