Fana: At a Speed of Life!

በሙስና ወንጀል በመንግስት ላይ 22 ነጥብ 75 ሚሊየን ብር ጉዳት ያደረሰው ተከሳሽ ገንዘቡ አንዲወረስ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሙስና ወንጀል በመፈፀም በመንግስት ላይ 22 ሚሊየን 725 ሺህ ብር ጉዳት ያደረሰው ተከሳሽ ገንዘቡ በመንግስት አንዲወረስ ተደርጓል፡፡
 
በአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም በመሳለሚያ ካዛንችስና አራዳ ቅርንጫፍ ከሚሰሩ ሰራተኞች ጋር በመመሳጠር በተፈጸመ የሙስና ወንጀል የተገኘ 23 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ገንዘብ በመንግስት አንዲወረስ መደረጉን የፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል።
 
ወንጀሉን የፈፀመው ግለሰብ ከዚህ በፊት በ11 ዓመት ፅኑ እስራትና በ65 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት አንዲቀጣ የተወሰነበት ሲሆን÷ ተከሳሹ በፈጸመው የሙስና ወንጀል ምክንያት ያገኘው ወደ 23 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ገንዘብም በመንግስት አንዲወረስ መደረጉ ተገልጿል።
 
ገንዘቡ አንዲወረስ ያደረገው በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ በወንጀል የተገኘ ሀብት ማስመለስ ዳይሬክቶሬት ጀኔራል ነው።
 
በመኪና ኪራይ አንዲሁም በሌሎች የንግድ ስራዎች ስራ ተሰማርቶ የሚገኘው ግለሰብ ከታህሳስ 2006 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 2008 ዓ.ም ባሉት ጊዚያት ውስጥ መሳለሚያ߹ካዛንችስና አራዳ ቅርንጫፍ በሚገኙ በአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም ከሚሰሩ ሰራተኞች ጋር በመመሳጠር በአንድ የመኪና ሊብሬ በተለያዩ የተቋሙ ቅርንጫፎች ብድር በመውሰድ߹በአንድ የመኪና ታርጋ በተለያዩ ግለሰቦች ስም ለዋስትና በማስያዝና ብድር በመወስድ አንዲሁም ለብድር በቂ ስንቅ የሌለው ቼክ በማቅረብ የሙስና ወንጀል ፈጽሞ በመንግስት ላይ ጉዳት በማድረስ ያገኘው ገንዘብ ህጋዊ ወለዱን ጨምሮ በመንግስት አንዲወረስ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ፀረ-ሙስና ወንጀል ችሎት መወሰኑ ይታወሳል።
 
በዚህም መሰረት ግለሰቡ በመንግስት እና ህዝብ ጥቅም ላይ ያደረሰው ጉዳት 22 ሚሊየን 725 ሺህ ከሀብቱ ላይ ተሰብስቦ ለመንግስት ገቢ መደረጉን በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ በወንጀል የተገኘ ሀብት ማስመለስ ዳይሬክቶሬት ጀኔራል አስታውቋል።
 
በመንግስት ሀብት ምዝበራው ተግባር ውስጥ የወንጀል ተሳትፎ የነበራቸው የተቋሙ ሰራተኞችም በወንጀል እንዲጠየቁ መደረጉ ተመላክቷል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.