አቶ አህመድ ሽዴ ከአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት ኃላፊ ጋር ውጤታማ ውይይት ማካሄዳቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ በአሜሪካና ኢትዮጵያ መካካል ስላለው የልማት ትብብር፣ በወቅታዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩ ኤስ ኤይድ) ዋና ኃላፊ ሳማንታ ፓወር ጋር ፍሪያማ ውይይት ማካሄዳቸው ተገልጿል።
በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ የተመራው የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን ከአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅቱ ዋና ኃላፊ ጋር ባደረገው ውይይት፥ በኢትዮጵያ የተከሰተው ግጭት ያስከተለውን ዘርፈ ብዙ ችግር፣ በአፍሪካ ቀንድ ስላለው ድርቅ እንዲሁም በዓለም ላይ የተፈጠረው የዋጋ መናር በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና ላይ በሚኖረው ተፅዕኖ ዙሪያ በስፋት መክሯል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት በሰጡት ማብራሪያ፥ የህዝቦችን አንድነት ማጎልበት፣ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነትን ማጠናከር፣ በግጭት ምክንያት ለተጎዱ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ ማድረስን እንዲሁም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት የመንግስት ዋነኛ ዓላማዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
አያይዘውም የተከሰተው ግጭት ከፈጠረው ሰብአዊ ቀውስ ባለፈ በርካታ ተፅዕኖ ማስከተሉንም አስረድተዋል።
መንግስት ግጭትን በማቆም ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠርና በኢትዮጵያ ሰላምን ለማረጋገጥ ቁርጠኛ መሆኑንም በዚህ ወቅት አረጋግጠዋል።
ሁለቱ ወገኖች በውይይታቸው ወቅት፥ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የሰብአዊ አገልግሎት መሳለጥ ሲባል በተወሰደው ግጭትን የማቆም እርምጃና በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች ያለምንም ገደብ ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ የተሰሩ ስራዎች ተነስተዋል።
በውይይታቸው የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት በቀጠናው የምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ እያደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ ስለሚቀጥልበት ሁኔታ መምከራቸውንም የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።