Fana: At a Speed of Life!

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተፈናቃይ ወገኖችን ከዕለት ድጋፍ ወደ መልሶ ማቋቋም ለማሸጋገር እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖችን ከዕለት ድጋፍ ወደ መልሶ ማቋቋም ለማሸጋገር እየተሰራ መሆኑን የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

የክልሉ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ታረቀኝ ታሲሳ ÷ በክልሉ ሶስት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ ተከስቶ በነበረው ችግር የተፈናቀሉ ወገኖች በመተከል ዞን እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

አብዛኞቹ ተፈናቃይ ወገኖች በጊዜያዊ መጠለያ እንደሚገኙ ያመለከቱት አቶ ታረቀኝ የዕለት ደራሽ ምግብን ጨምሮ አቅም በፈቀደ መጠን ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

እየጣለ በሚገኘው ዝናብ ተፈናቃዮቹ ለተላላፊ በሽታዎች እንዳይጋለጡ ጊዜያዊ መጠለያን ለማጠናከር እና መድሃኒትን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎችን ለማቅረብ ትኩረት እንደሚሰጠው አስታውቀዋል፡፡

በአሶሳ እና ካማሺ ዞኖች እንዲሁም በማኦ ኮሞ ልዩ ወረዳ ግን የዕለት ደራሽ ድጋፍ በጸጥታ ችግር ምክንያት እየተስተጓጎለ በመሆኑን ድጋፉን በሚገባ ማቅረብ አለመቻሉን ጠቁመዋል፡፡

መልሶ ማቋቋሙ ከፍተኛ የሰው ሃይል፣ በጀት እና እስከ አምስት ዓመት እንደሚፈጅ በጥናት ተለይቷል ብለዋል፡፡

ይህ ደግሞ በክልሉ መንግስት አቅም ብቻ የሚከናወን ባለመሆኑ የፌደራል መንግስት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እገዛቸውን እንዲያጠናከሩ ኮሚሽነሩ ጠይቀዋል፡፡

የመልሶ ማቋቋሙ እቅድ በአጭር ጊዜ ወደ መሬት እንዲወርድ የክልሉን ሠላም አስተማማኝ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው ለዚህም የክልሉ መንግስት እየሰራ መሆኑን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.