Fana: At a Speed of Life!

ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ ድርቅ ጉዳት ላደረሰባቸው ዜጎች የሚደረገው ድጋፍ መጠናከር አለበት አሉ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ  በኢትዮጵያ ከአሜሪካ አምባሳደር እና የዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ጋር ባደረጉት ውይይት በክልሉ በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የሚደረገው ድጋፍ መጠናከር እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ ዛሬ በክልሉ ጉብኝት ካደረጉት በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚ አምባሳደር ጃኮብሰን እና የዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ካትሪን ሩሴል ጋር በመሆን በሸቤሌ ዞን ጎዴ ከተማ ተገኝተው የድርቅ ተጎጂዎችን  የጎበኙ ሲሆን÷ ድርቁን ለመከላከል በቀጣይ በሚደረጉ ዘላቂ ሥራዎች ላይ መክረዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ ከሁለቱ ኃላፊዎች ጋር ባደረጉት ውይይት፥ በክልሉ በድርቅ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች እየተደረገ ያለው ድጋፍ መጠናከር እንደሚገባው መግባባት ላይ መድረሳቸውንም በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል።

ክልሉ በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት ምንም ዓይነት የበልግ ዝናብ አለማግኘቱን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ የድርቅ ሁኔታው የፈጠረው አሉታዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ የሚያስከትለውን ችግር ለመቋቋምና ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ፈጥኖ ለመታደግ የሚደረገውን ሰብዓዊ ድጋፍ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

ድርቁ ያስከተለውን ተጽዕኖ ለመቋቋምና ፈጣን ምላሽ በመስጠት ድጋፉ በዓይነት መጠናከርና በመጠንም መጨመር እንደሚገባው ነው የተጠቆመው።

በጎዴ ከተማ በተካሄደው የመስክ ጉብኝት÷ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድን ጨምሮ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚ አምባሳደር ጃኮብሰን፣ የዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ካትሪን ሩሴል፣ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ሁሴን ቃሲም፣ የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር ቢሮ ኃላፊ አቶ አሕመድ ያሲን ኢብራሂም ተገኝተዋል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.