Fana: At a Speed of Life!

የምርምርና የልህቀት ማዕከል ዩኒቨርሲቲዎች የግብዓት እጥረት አንዳጋጠማቸው ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በከፍተኛ ትምህርት እና ስልጠና ፍኖተ ካርታ መሰረት ሦስት የምርምር እና የልህቀት ማዕከል የሆኑት የጎንደር፣ ባሕር ዳር እና ጅማ ዩኒቨርሲቲዎች ለምርምር የሚያስፈልጉ ቁሳቁስ ጨምሮ የገንዘብ እጥረት አለብን ብለዋል።
ሦስቱም የምርምርና የልህቀት ማዕከል ዩኒቨርሲቲዎች÷ የገጠማቸውን የግብዓት እጥረት ለመፍታት የተለያዩ አማራጮችን እየፈለጉ መሆናቸውን ነው ለፋና ብሮድካስንግ ኮርፖሬት የገለጹት፡፡
የጎንደር ዩንቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን÷ ዩኒቨርሲቲው የምርምር ሥራዎችን በማጠናከር ኮቪድን መከላከል የሚያስችል እና የአርሶ አደሩ ህይወት ጋር የተያያዙ ችግር ፈቺ ምርምሮችን እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የጅማ ዩኒቨርሲቲ የምርምና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጻነት ወርቅነህ÷ ዩኒቨርሲቲው የምርምር ዩኒቨርሲቲ ሆኖ ከተመረጠ ጊዜ ጀምሮ ተልዕኮውን መወጣት የሚያስችል ሥራ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ተልዕኮውን በአግባቡ ለመወጣት ግን የሰው ኃይል እና ገንዘብ እጥረት እንደገጠመው ገልጸው÷ ችግሩን ለመቅረፍ የሚያስችል ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ተስፋዬ ሽፈራው፥ የማሀብረሰቡን ችግር የሚፈቱ የምርምር ሥራዎችን ለማከናወን የውል ስምምነት ተወስዶ እየተሰራ ቢሆንም እነዚህን የምርምር ሥራዎች ለማከናወን ዩኒቨርሲቲው የግብዓት እጥረት አጋጥሞታል ብለዋል፡፡
የሚሠሯቸው የጥናት እና የምርምር ሥራዎች ከማህበረሰቡ ተሻግረው ዓለም አቀፋዊ ችግር ፈቺ እንዲሆኑ፥ የተቀናጀ ሥራ፣ ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያስፈልግ ሦስቱም የምርምርና የልሕቀት ዩኒቨርሲቲዎች አመላክተዋል፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት አካዳሚ ጉዳዮች ዳሬክተር ዶክተር ኢባ መጀና በበኩላቸው÷ በምርምር የተለዩ ዩኒቨርሲቲዎች መሥራት ያለባቸውን እና የተመደቡበትን መነሻ በማድረግ ያሉባቸውን ችግሮች መፍታት የሚያስችል መርሐ ግብር ተዘጋጅቶ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በሲሳይ ጌትነት
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.