የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ኢኮኖሚያዊ ጫናን የተሻገረችው አካታች እና ዘላቂ የልማት ግቦችን በመከተሏ ነው – ዶክተር ሊያ ታደሰ

By Alemayehu Geremew

April 26, 2022

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዘላቂ የልማት ግቦች ስኬታማ የሚሆኑት እና ሀገራት ከኢኮኖሚያዊ ጫና ማገገም የሚችሉት አካታች እና ዘላቂ መርሆዎችን ሲከተሉ እንደሆነ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ፡፡

ዶክተር ሊያ ታደሰ በተባበሩት መንግስታት የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ምክር ቤት ዘላቂ የልማት ግቦችን በገንዘብ ለመደገፍ ያለመ ፎረም ላይ ተካፍለዋል።

በዚህ ወቅትም ዶክተር ሊያ የኢትዮጵያን ተሞክሮ ለአብነት ማንሳታቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል።

ኢትዮጵያ የኮቪድ 19ኝ ወረርሽኝ፣ በግጭት ወቅት ያጋጠመውን ኢኮኖሚያዊ ጫና፣ ድርቅ በሀገሪቷ ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ፣ እንዲሁም ሌሎችን ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች መቋቋም የቻለችው ሁሉንም ዜጋ ያሳተፈ ዘላቂ የልማት ግብ መርህ በመከተሏ ነው ብለዋል፡፡

የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ትብብር በመሻት ሀገራዊ ዕቅዶችን ጎን ለጎን ማስኬድ፣ የውጭ ሀገራትን የኢኮኖሚ ድጋፍ የሀገርን ኢኮኖሚ ለመደገፍ በአግባቡ መጠቀም እንዲሁም በብድር ለተገኙ ድጋፎች እፎይታ የሚሰጡ ዘላቂ መፍትሄዎችን ማፈላለግ ኢትዮጵያ ዘላቂ የልማት ግቧን ለማሳካት የሄደችባቸው ሥልቶች እንደሆኑም አንስተዋል።