Fana: At a Speed of Life!

ላሊበላ የጎብኚ እንቅስቃሴ እርቋት በመቆየቷ የከተማዋ ነዋሪዎች ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን ተናገሩ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የጎብኚ እንቅስቃሴ እርቆት በመቆየቱ የቅርሱ አገልጋዮች፣ ጠባቂዎችና የከተማዋ ነዋሪዎች ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን ተናግረዋል፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በስፍራው ባደረገው ምልከታ ይህን ማረጋገጥ ችሏል።

የቅርሱ አገልጋዮች እንዳሉት ቀድሞ የከተማዋን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ቀንሶ የነበረው የኮቪድ19 ወረርሽኝን ተከትሎ የተከሰተው ጦርነት ቱሪዝሙን ወደ አዘቅጥ ከቶታል፣ በቱሪዝሙ ላይ ኑሯቸው የተመሰረተው የቤተክርስቲያኗ አባቶች፣ አገልጋዮች እና የከተማዋ ነዋሪዎች ለከፋ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ መዳረጋቸውን ገልጸዋል።

በሽብር ቡድኑ ውድመት የደረሰባቸው የሆቴል ባለቤቶች እና ስራ አስኪያጆች የደረሰው የመሰረተ ልማት ውድመት ጎብኚዎችን በማራቁ ቀድሞ የሚያስተናግዱት በርካታ ደንበኞች አሁን ላይ አለመኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

ነዋሪዎችም የመብራት፣ የውሃ እና የወደሙ ሌሎች መሰረተ ልማት ለከፋ ችግር እንደዳረጋቸው ተናግረዋል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ጣቢያችን ያነጋገረው የቱሪዝም ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም በጦርነቱ የወደመውን የላሊበላ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ አገልግሎት እንዲመለስ የሰራውን ስራ ጠቅሶ በቀጣይም የተያዙ እቅዶች መኖራቸውን ገልጿል።

በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አማካሪ የሆኑት አቶ ጌትነት ይግዛቸው÷ የጎብኚ ፍሰቱ ከላሊበላ መቀነሱ ያስከተለው ተጽእኖ ቀላል አለመሆኑን አስረድተዋል።

ጎብኚዎች ወደ ከተማዋ እንዲመለሱ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ስራዎች መሰራት አለባቸው ብለዋል።

የከተማዋ ሰላም የተጠበቀ መሆኑን ለማስተዋወቅ እና ጎብኚዎችን ለመጥራት፣ የወደሙ መሰረተ ልማቶች በተለይም የመብራት እና የውሃ አቅርቦትን በአፋጣኝ መመለስ እንደሚገባም ገልጸዋል።

በሀገሪቱ በቱሪዝም ዘርፉ የሚንቀሳቀሱ የዘርፉ ተዋንያንም የከተማዋን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለመመለስ በቅንጅት መስራት አለባቸው ነው ያሉት።

በቆንጂት ዘውዴ

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.