Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር ወደ አዲስ ምዕራፍ እንድትሸጋገር ከኮሚሽኑ የላቀ ሚና ይጠበቃል – አፈ ጉባዔ ታገሠ ጫፎ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ አዲስ ምዕራፍ እንድትጀምር እና ወደ ትክክለኛው ብሔራዊ መግባባት እንድትሸጋገር ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የላቀ ሚና እንደሚጠበቅ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሠ ጫፎ ተናገሩ፡፡

ሀገራዊ ትርጉም ያላቸውን ተግባራት ከማከናወን አንጻር ኮሚሽኑ በቀጣዮቹ 3 ዓመታት የሚያከናውናቸውን ተግባራት የሚያመላክት ፍኖተ ካርታ፣ የግብ ማስፈጸሚያ ስትራቴጂ፣ የአጀንዳ አቀራረጽ ሂደት እና አጠቃላይ ሀገራዊ ምክክሩ እንዴት መጀመር እንዳለበት የሚያሳይ ዕቅድ ማዘጋጀት እንዳለበት አፈ ጉባዔው አሳስበዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ሎሚ በዶ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ዐቢይ ዓላማ ሀገርን እና ሕዝብን መታደግ መሆኑን ገልጸው÷ ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ዜጎች ለአስከፊ ችግር የተጋለጡ መሆናቸው ታውቆ የኮሚሽኑ ቅድሚያ አጀንዳ ሰላምን ማስፈን ሊሆን እንደሚገባ እና ሥራውም መፋጠን አለበት ብለዋል፡፡

የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ኮሚሽኑ ሥራዎቹን በአራት ምዕራፎች ከፋፍሎ እየሠራ መሆኑን ገልጸው÷ የቅድመ ዝግጅት፣ የምክክር እና ክንውን እንዲሁም የምክክር ውጤቶች መተግበሪያ ክትትል ምዕራፎች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ስራ የተሳካ እና ውጤታማ እንዲሆን ከአገር ውስጥ ተቋማት እና ከውጭ አገራት ጋር የልምድ ተሞክሮ እየተቀመረ መሆኑን ገልጸው÷ ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ግቡን እንዲመታ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከመገናኛ ብዙኃን ኃላፊዎች ጋር ውይይት ተደርጓል ብለዋል፡፡

አያይዘውም ኮሚሽኑ አዲስ ከመሆኑ አንጻር የግልጸኝነት፣ የተለያዩ አካላት ጣልቃ ገብነት እና ለዘመናት የተከማቹ አጀንዳዎች መኖራቸው እንደ ተግዳሮት የሚነሱ መሆናቸውንም አብራርተዋል፡፡

ምክትል ኮሚሽነር ዶክተር ተገኘወርቅ ጌቱ በበኩላቸው የኮሚሽኑ አጀንዳ ከሕዝብ የመነጨ መሆን እንዳለበት ጠቁመው÷ ሁሉንም ዜጎች ያካተተ መረጃ መሰብሰብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ÷ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ውጤት የዴሞክራሲን ባህል የሚያጸና፣ ምህዳሩን የሚያሰፋ እንዲሁም የዴሞክራሲ ሥርዓት ትግበራን ለማረጋገጥ የሚያግዝ ነው ማለታቸውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.