Fana: At a Speed of Life!

ኮሚሽኑ ከተጣለበት ሀገራዊ ሀላፊነት አንጻር የዜጎችን ተሳትፎ ባረጋገጠ መልኩ ነጻ መሆን ይገባዋል – የፖለቲካ ፓርቲዎች

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ከተጣለበት አገራዊ ሀላፊነት አንጻር የሁሉንም ዜጎች ተሳትፎ ያረጋገጠ እና ከወገንተኝነት የጸዳ መሆን ይገባዋል ሲሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተናገሩ፡፡

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ፓርቲ እና የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ፥ በቀጣይ በኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን አማካኝነት በሚደረጉ አገራዊ ውይይቶች ላይ የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ መዘጋጀታቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ( ኢዜማ) የአገራዊ ምክክር ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እዮብ መሳፍንት፥ ፓርቲው ለጉዳዩ ከሰጠው ሰፊ ትኩረት አንጻር በፓርቲው ውስጥ ይህን ጉዳይ ብቻ የሚከታተል ኮሚቴ ተቋቁሟል ብለዋል፡፡

አንደ ፓርቲም እንደ ሀገርም ብሄራዊ ምክክር ሊኖረው ስለሚችለው ጠቀሜታም ሰነዶችን ማዘጋጀቱን እና በቅርቡም ይህን ለፓርቲው አባላት እና ደጋፊዎች ይፋ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚአብሄር በበኩላቸው፥ ፓርቲው ለምክክር አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆኑን አመላክተዋል።

አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በጠየቀው ጊዜ ሊያቀርበው የሚችለውን የውይይት አጀንዳዎችን የያዘ ሰነድ መቅረፁንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አህመዲን በደዊ ÷ ፓርቲው ምክክር ሁሉን አሳታፊ እና ከወገንተኝነት የጸዳ ሆኖ እንዲካሄድ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው አስታውቀዋል።

ከዚህ አንጻር አባላቱም ሆኑ ደጋፊዎቹ በውይይት ሰፊ ተሳትፎ ለማድረግ የሚያስችላቸውን እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ነው የገለጹት።

በአጠቃላይ ኮሚሽኑ ከተጣለበት ሰፊ አገራዊ ሀላፊነት አንጻር የሁሉንም ዜጎች ተሳትፎ ያረጋገጠ እና ከወገንተኝነት የጸዳ መሆን እንደሚገባው ፓርቲዎቹ አንስተዋል፡፡

ኮሚሽኑ እያንዳንዱ እንቅስቃሴው በህዝብ የሚታወቅበት የግንኙነት መንገድ መፍጠር እንደሚኖርበትም ነው ያሳሰቡት፡፡

በትዕግስት አብርሃም

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.