Fana: At a Speed of Life!

የአድዋ ድል በዓል ኢትዮጵያውያን በየትኛውም ወቅት በሀገር ልዕልና፣ መብት እና ነፃነት ዙሪያ እንደማይደራደሩ ያሳየ ነው – ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 124ኛው የዓድዋ የድል በዓል በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በዛሬው ዕለት ተከብሯል።

የድል በዓሉ የጣሊያን ወራሪ ድል በተደረገበት የዓድዋ ተራሮች ስርም በተለያዩ ስነ ስርዓቶች ተከብሯል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂምና የትግራይ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

ፕሬዚዳንቷ በበዓሉ ላይ ባደረጉት ንግግር የዓድዋ ድል በዓል ቅኝ ግዛትን ማሸነፍ እንደሚቻል ያበሰረ እና የነፃነት ጮራ እንዲፈንጥቅ ያደረገ ነው ብለዋል።

በዓድዋ ድል በዓል ከማንኛውም የውስጥ ችግር በላይ ለኢትዮጵያ ነፃነት ትኩረት በመስጠት ነፃ ሀገር ማቆየት ተችሏልም ነው ያሉት።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ የዓድዋ ድል በዓል ስንደማመጥ እና ስንነጋገር የማንወጣው አረንቋ እንደሌለ ማሳያ መሆኑንም አንስተዋል።

በዓሉ ኢትዮጵያውያን በየትኛውም ወቅት በሀገር ልዕልና፣ መብት እና ነፃነት ዙሪያ እንደማይደራደሩ ያሳየ መሆኑንም ተናግረዋል።

የአድዋ የድል በዓል በየዕለቱ ልንመራበት እና በህይወታችን ልንጠቀምበት የሚገባ መሆን እንዳለበትም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ሰላሟ የተጠበቀ፣ ከድህነት የወጣች እና አንድነቷ የተጠበቀ መሆን እንዳለባትም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በበኩላቸው፥ የአድዋ የድል በዓል ማንኛውም ህብረተሰብ ሊገመት የማይችል ውጤት ማስመዝገብ እንደሚችል ጥሩ ምሳሌ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከዓድዋ ድል የምንወስደው ትምህርት ዘመናዊ መሳሪያ መታጠቅ አለመታጠቅ፣ የወታደር መብዛት ማነስ፣ መሰልጠን አለመሰልጠን የየራሳቸው አወንታዊና አሉታዊ ጫና ቢኖራቸውም ህዝባዊ አንድነትና ፅናት ምን ጊዜም የድል ባለቤት መሆኑ እሙን ነው ብለዋል በንግግራቸው።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ወጣቱ ትውልድ የሀገርን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ እና ሰላምን ለማስፈን መታገል እንዳለበት አሳስበዋል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው፥ የዓድዋ ድል ከድል በላይ ሆኖ የድሎች ቁንጮ በመሆን የሚጠቀስ መሆኑን አውስተዋል።

ሚኒስትሯ ኢትዮጵያ በዓድዋ የድል በዓል ምክንያት ለመላው የጭቁን ህዝቦች የነፃነት ተምሳሌት ሆናለች ነው ያሉት።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.