Fana: At a Speed of Life!

ብልፅግና ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤውን በተመለከተ ተጨማሪ ሰነዶች እና መረጃዎችን እንዲያቀርብ ምርጫ ቦርድ ጠየቀ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 19 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ብልፅግና ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤውን በተመለከተ ተጨማሪ ሰነዶች እና መረጃዎችን እንዲያቀርብ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጠይቋል።
ቦርዱ ሚያዝያ 13 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ ፓርቲው ያቀረባቸውን የጠቅላላ ጉባኤ ሰነዶች እና ጠቅላላ ጉባኤውን በታዘቡት የቦርዱ ተወካዮች የቀረበውን ሪፖርት መመርመሩን አስታውቋል።
ይሁንና የጠቅላላ ጉባኤውን ሂደት፣ በጉባኤው የተላለፉ ውሳኔዎች እና የተደረጉ ምርጫዎችን በተመለከተ ከሕጉ አንጻር ለወሰን ተጨማሪ ሰነዶች እና መረጃዎችን ማየት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁሟል።
በሆኑም ፓርቲው ምርጫ ቦርድ በዝርዝር ያስቀመጣቸውን ጉዳዮች ከሚያዚያ 25 ቀን 2014 ዓ.ም በፊት ለቦርዱ እንዲያቀርብ አሳውቋል።
ቃለ ጉባኤን በተመለከተ፣ በጠቅላላ ጉባኤ ቃለ ጉባኤው ላይ የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባው ምልአተ ጉባኤ ተሟልቷል ቢባልም በግልፅ የጠቅላላ ባኤው ተሳታፊ አባላት ብዛት ስላልተቀመጠ ተገልፆ እንዲቀርብ፤ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የተጠቆሙበት ሂደት፣ እነማን እንደተጠቆሙ፣ ከተጠቆሙት ውስጥ የተመረጡት አባላት እያንዳንዳቸው በስንት ድምፅ እንደተመረጡ በጠቅላላ ጉባኤ ቃለ ጉባኤ ውስጥ ያልተገለፀ በመሆኑ ይሄው ተካትቶ እና ተረጋግጦ እንዲቀርብ፤ በፓርቲው የቀረበው ጠቅላላ ጉባኤ ቃለ ጉባኤ በፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ተፈርሞ እንዲቀርብ፤ የማዕከላዊ ኮሚቴው ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትን የመረጠበትን ሂደትየሚያሳይ የማዕከላዊ ኮሚቴ ቃለ ጉባኤ ስላልቀረበ እንዲቀርብ ጠይቋል።
የፖርቲው መተዳደሪያ ደንብን በተመለከተ ደግሞ በመተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 18/3 መሠረት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ብዛት እና ስብጥርን በተለከተ የወጣ የአፈፃፀም መመሪያ ካለ የመመሪያውን ኮፒ ማዕከላዊ ኮሚቴው መመሪያውን ካፀደቀበት ቃለ ጉባኤ ጭምር እንዲቀርብ ምርጫ ቦርድ ለፓርቲው በጻፈው ደብዳቤ ጠይቋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.