በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ በማበርከት ላይ የሚገኙ አካላት በሰላም ግንባታ ላይም ሊያተኩሩ ይገባል – ዶ/ር ይልቃል ከፋለ
አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 19 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ በማበርከት ላይ የሚገኙ አካላት በሰላም ግንባታ ላይም እንዲያተኩሩ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ጠየቁ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ልዑካንን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በዓለም የምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ክላውድ ጂቢዳር የተመራው የልዑካን ቡድን እስካሁን በክልሉ እያከናወናቸው ባሉና በቀጣይ የክልሉን መንግስት የትኩረት አቅጣጫ አውቆ ለመደገፍ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ገለጻ አቅርቧል።
በፕሮግራሙ አማካኝነት በጦርነቱና በከፊል የተፈጥሮ አደጋ ለተፈናቀሉ ከ1 ሚሊየን 872 ሺህ በላይ ወገኖች ካለፈው መስከረም ወር ጀምሮ በልዩ ልዩ ስልቶች የዕለት ደራሽ የምግብ እህል እየደገፈ እንደሚገኝ ተነስቷል።
በክልሉ ከ11 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ወገኖች ድጋፍ የሚሹ መሆናቸውን ስለተገነዘብን የክልሉን መንግስት ፍላጎት ባገናዘበ ሁኔታ የድርሻችንን ከመወጣት ባሻገር የችግሩን ስፋት ለሌሎች ለጋሾችም ለማሳወቅ የሚያስችል መረጃ ለማግኘት ውይይት ማካሄድ ማስፈለጉን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
የዓለም የምግብ ፕሮግራም በክልሉ በ23 ወረዳዎች ድጋፍ ከሚሰጣቸው የተጠቀሱ ወገኖች መካከል በ129 ትምህርት ቤቶች የምግብና አገልግሎት የሚሰጣቸው 45 ሺህ ተማሪዎች ይገኙበታል ተብሏል።
በ221 ሚሊየን ብር ለ200 ሺህ አርሶ አደሮች የምርጥ ዘር አቅርቦት እና ለእርባታ የሚሆኑ የቤት እንስሳትን በማቅረብ የሚደገፉ እንዳሉም ነው የተጠቀሰው።
ለ85 ሺህ 600 ነፍሰ ጡርና አጥቢ እናቶች እንዲሁም ከአምስት ዓመት በታች ዕድሜ ላላቸው ህፃናት የአልሚ ምግብ ድጋፍ እየቀረበ መሆኑም ታውቋል።
ዶክተር ይልቃል ከፋለ በበኩላቸው÷የዓለም የምግብ ፕሮግራም በክልሉ እስካሁን ላበረከተውና እያበረከተ ላለውም አስተዋኦ ምስጋና አቅርበዋል።
በክልሉ ከቀን ቀን የሚስተዋለው ድጋፍ የሚሹ ወገኖች ቁጥር እያሻቀበ ከመሄዱ አኳያ ፕሮግራሙ መልካም ተግባራቶቹን አስፍቶ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን ከርዕሰ መስተዳድሩ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ለችግር የተጋለጡ ወገኖች በዘላቂነት ኑሯቸውንመምራት እንዲችሉ ለጋሽ አካላት በስዕብና እና ሰላም ግንባታ ላይ የተፈናቀሉ ወገኖች ሰፊ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በዚህም ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩም ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!