ሃይማኖት የሰላም እንጂ በምንም ምክንያት የግጭት መንስኤ ሊሆን አይችልም- የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ
አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 19 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሃይማኖት የሰላም እንጂ በምንም ምክንያት የግጭት መንስኤ ሊሆን አይችልም ሲል የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በትናንትናው ዕለት በአማራ ክልል በጎንደር ከተማ የተከሰተውን ክስተት አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።
በመግለጫውም የተፈፀመው ግድያ፣ የመስጊድ ቃጠሎ እንዲሁም የሙስሊም ግለሰቦች ንብረት ውድመት እና ዘረፋ በሃይማኖት እጅግ የከፋ ሃጢያት እና በፈጣሪም ዘንድ የሚያስጠይቅ ፀያፍ ተግባር መሆኑን አንስቷል፡፡
ጉባኤው ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ሃይማኖት የሰላም እንጂ በምንም ምክንያት የግጭት መንስኤ ሊሆን አይችልም!
ሃይማኖት የሰላም፣ የአብሮነትና የፍቅር መሠረት ናት፡፡ በዓለም ላይ ያሉ ሃይማኖቶች በሙሉ ፍቅርን፤ ሰላምን፤ አብሮነትን፤ በጋራና በትብብር ማደግን እንዲያስተምሩ ፈጣሪ ኃላፊነት የሰጣቸው የተከበሩ ተቋማት ናቸው፡፡ ይህን የተጣለባቻውን መለኮታዊ ተልዕኮ በአግባቡ ለመወጣት በሚችሉት አቅም ጥረት ሲያደርጉ ይታያል፡፡ ሆኖም የሃይማኖት አስተምህሮን በተቃረነ መንገድ በማሰብና በማቀድ ልዩነትን መሠረት ያደረገ ስድብንና ጥላቻን የሚያስፋፉ አካላቶች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ hዚህም ባለፈ በቀላሉ በመነጋገርና በመወቃቀስ ችግሮች መፍታት እየተቻለ ቀላል ጉዳዮችን መነሻ በማድረግ ክቡር የሆነውን የሰውን ሕይወት እስከማጥፋት የሚደርሱ ከባድ ተግባራትን መፈጸም በሃገራችን ኢትዮጵያ መስማትና ማየት እየተለመደ መጥቷል።
በጎንደር ከተማ በሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ ሚያዝያ 18 ቀን 2014 ዓ.ም የተፈፀመው የግድያ፤ የመስኪድ ቃጠሎ የሙስሊም ግለሰቦች ንብረት ውድመትና ዘረፋ በሃይማኖት እጅግ የከፋ ሃጢያት ሲሆን በፈጣሪም ዘንድ የሚያስጠይቅ ፀያፍ ተግባር ነው፡፡ የሃገራችን ሕዝብ ልዩነትን በማክበር በጋራ ጉዳዮች ላይ በመደጋገፍና በመተባበር ለዘመናት የኖረበትን የተከበሩ እሴቶችና ታሪኮች የሚያጎድፍ እጅግ አሳዛኝ ተግባር ነው፡፡ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የደረሰውን የሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት ዜና የሰማው በታላቅ የልብ ስብራት ሲሆን ድርጊቱንም አምርሮ ያወግዛል፡፡ የሰውን ሕይወት እንዲሁም በብዙ ልፋትና ጥረት የተገኘን የንፁሃንንና የሃገርን ሃብት በማውደም ለግጭት ምክንያት የሆኑ ችግሮችን መፍታት እንደማይቻል ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል፡፡ የዚህ ዓይነት ተግባር
ተደራራቢ ችግሮችን ከማስከተሉም ባለፈ ምንም አይነት አወንታዊ ውጤት ሊያመጣ እንደማይችል በመረዳት ሁሉም ዜጋ ችግርን በጥፋት ለመፍታት ከሚደረግ ጥረት ሊመለስ ይገባል፡፡
የሃገራችን የፌዴራልና የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የተፈጠረውን ችግር በማባባስ በሕዝባችን መካከል ተጨማሪ ደም መፍሰስን ለማምጣት እየሠሩ ያሉትን አካላት በአግባቡ በመለየት ከጥፋት ጉዞአቸው እንዲመለሱ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ እንዲሁም የሰው ሕይወት በማጥፋትና ንብረት በማውደም ተግባር ላይ የተሳተፉና ትብብር ያደረጉትን አካላት በሕግ አግባብ በማጣራት አስተማሪና ሕጋዊ እርጃ በመውሰድ ለሕብረተሰቡ እንዲያሳውቁ በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡
የጎንደር ከተማና በአካባቢው የምትኖሩ ነዋሪዎች እንዲሁም የሃገራችን የሃይማኖት ተከታዮች የተፈጠሩና የሚፈጠሩ ችግሮችን በኃይል ለመፍታት ከመሞከር በመቆጠብ ሃይማኖታዊ አስተምህሮን መሰረት በማድረግ በተረጋጋ መንፈስ በምክክር ችግሮችን ለመፍታት የበኩላችሁን ጥረት እንድታደርጉ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
ደም ደምን እንደሚጠራ በመገንዘብ ከደም ከጥላቻ ከቂም በቀል የነፃች ሁሉንም የማሕበረሰብ ክፍል በእኩል የምታስተናግድ ሃገር ለመገንባት ዜጎች ሁሉ የድርሻችሁን እንድትወጡና የሃገራችን የሃዘንና የለቅሶ ጊዜ እንድናሳጥር በፈጣሪ ስም እንጠይቃለን።
በሃጋራችን የምትገኙ የሃይማኖት ተቋማት በሙሉ ለሕዝባችን ፍቅርን፣ አብሮነትን፣ በአጠቃላይ ከሰው ልጆች ሁሉ ጋር በሰላምና በመከባበር መኖር እንደሚያስፈልግ በስፋትና በጥራት እንድታስተምሩ አደራ እንላለን፡፡
ይህም የሃይማኖት ተቋማት የተመሠረቱበት ዓብይ ዓላማ መሆኑን በመገንዘብ ከሃይማኖት አስተምህሮ በተቃረነ መንግድ በመጓዝ ጥላቻና ከፍ ያለ ጉዳት በሚያስከትሉ ተግባራት ላይ እየተሳተፉ ያሉትን አካላት የማረምና የመመለስ ተግባራችሁን ከምንጊዜውም በላይ አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ
ሚያዝያ 19 ቀን 2014 ዓ.ም
አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ