Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ለዘንድሮው የፊቼ ጨምበላላ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 20 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሲዳማ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ “ፊቼ ጫምባላላ” በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው በሲዳምኛ ቋንቋ ባስተላለፉት መልዕክት÷የሲዳማ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል ለሚያከብሩ ሁሉ መልካም የፊቼ ጨምበላላ በዓል ተመኝተዋል።
 
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው የሲዳማ ብሔር በሀገሪቱ ከሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦች ውስጥ አንዱ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ከእነዚህ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በመስማማት አብሮ እየኖረ የራሱንም ባህልና ታሪክ እያበለጸገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
 
በአገራዊ አብሮነት ውስጥ የራሱን ውብ ባህሉን እያከበረና እያንጸባረቀ ለብዙ ዘመናት በደስታ እየኖረ መቆየቱን እና ዛሬም የራሱ የዘመን መለወጫ ጠብቆ እየኖረ እንደሚገኝ ነው የገለፁት።
 
የአገር ሽማግሌዎች ወይም የሲዳማ አያንቶዎች አብረው በመሰባሰብ የጨረቃንና የከዋክብቶችን የተፈጥሮ ኡደት በማጥናትና በመመልከት አዲስ ዓመት የሚገባበትን ቀን ማየታቸውና መቼ እንደሆነ ለማወቅ መቻላቸው የሚደነቅ መሆኑን አመልክተዋል።
 
የፊቼ ጨምበላላ በዓል ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ከአያትና ቅድመ አያቶች ሲወርድ ሲዋረድ እየተወረሰ መምጣት ብቻ ሳይሆን በአሁኑ ጊዜ ከአገር አልፎ በዓለም ደረጃ ልዩ የህዝብ ቅርስ ሆኖ በዩኔስኮ በማይዳሰስ ቅርስ መመዝገብ መቻሉም የህዝብ እውቀት ዘመንና አገር ተሻጋሪ ለመሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል።
 
ይህ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ የመጣው ባህል ዝርዝር ትርጉሙን ስንመለከት ሰላም፣ አብሮነትና ፍቅርን የሚያመላክት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ በዚህ አንጋፋ ባህል ምክንያት አጎረባች የሆኑት ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ወንድሞቹ ጋር በመተባበርና አብሮነቱን በማጠናከር አብሮ መኖሩንም አድንቀዋል።
 
ፊቼ ፍቅርና አንድነትን የሚያንጸባርቅ በመሆኑ በጎረቤቱና በአካባቢው ያሉትን የሌላ ብሔር ተወላጆች ወንድሞቹንም የሚያቅፍበት ድንቅ ባህል እንደመሆኑም ሌላውን ብሔር ብሔረሰብ ወንድሞቹ ጋር በጋራ በመሆን ለአዲስ የብልጽግና ጉዞ መሳለጥ እንዲጠቀምበት ነው ጥሪ ያቀረቡት።
 
ህዝቡ አዲስ አመትን ለቀጣይ መለወጥ፣ የኑሮ መሻሻልና ከችግር የመላቀቅ ዓመት ለማድረግ ጠንክሮ የሚሰራበት ወቅት መሆኑንም አስገንዝበዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.