ስፓርት

የፕሪሚየር ሊጉ የዲስፕሊን ኮሚቴ በባሕር ዳር ከተማው አጥቂ ሁሴን ማውሊ የቅጣት ውሳኔ አስተላለፈ

By ዮሐንስ ደርበው

April 28, 2022

 

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የዲስፕሊን ኮሚቴ በባሕር ዳር ከተማው አጥቂ ሁሴን ማውሊ ላይ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

የሊጉ የዲስፕሊን ኮሚቴ የ21ኛ ሣምንት መርሐ ግብር ከመጀመሩ በፊት በሣምንቱ በተከሰቱ የዲስፕሊን ግድፈቶች ላይ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

በዚሁ መሰረት መከላከያ ከባሕር ዳር ከነማ አቻ በተለያየበት ጨዋታ÷ የባሕር ዳር ከነማው አጥቂ ሁሴን ማውሊ በተከላካዩ ኢብራሂም ሁሴን የጨዋታ እንቅስቃሴ በሌለበት በእግሩ ላይ በመቆም ጉዳት ማድረሱ እና ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላም አጥቂው ሁሴን ማውሊ የተከላካዩን አንገት በማነቅ መገፍተሩ በተንቀሳቃሽ ምስል ተረጋግጧል፡፡

ተጫዋቹ በፈፀመው ጥፋት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መመሪያ መሰረት አጥቂው ሁሴን ማውሊ 4 ጨዋታ እንዲታገድ እና ተጨማሪ 3 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍል ተወስኗል፡፡

የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 20ኛ ሣምንት ጨዋታዎች ቀደም ሲል መጠናቀቃቸውን ተከትሎ የ21ኛ ሣምንት ጨዋታዎች በነገው ዕለት በአዳማ ሣይንስ እና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የሚጀምሩ ይሆናል፡፡