የጋምቤላ ክልል ለመኸር ወቅት የሰብል ልማት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው – የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጋምቤላ ክልል ለመኸር ወቅት የሰብል ልማት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮ ሃላፊው አቶ አጃክ ኡቻላ እንደገለጹት÷ በክልሉ በዘንድሮ የመኸር እርሻ ከ148 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በልዩ ልዩ የሰብል ዓይነቶች በመሸፈን ከአራት ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየተሠራ ነው፡፡
ለዚህም የመኸር እርሻ ልማቱን ውጤታማ ለማድረግ በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች የአመራርና የባለሙያ ስምሪት መከናወኑን ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም የበልግ አብቃይ በሆነው የማጃንግ ዞን ቀድመው በተዘሩ ሰብሎች መሸፈናቸውን ጠቁመው÷ በአኝዋሃና በኑዌር ዞኖችም ሰፊ የማሳ ዝግጅት ተደርጓል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡
የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊና የመንግስት ተጠሪ አቶ ሯች ባየክ በበኩላቸው÷ ሁሉም የክልሉ ማህበረሰብ በመኸር የግብርና ልማቱ እንዲረባረብ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አርሶ አደሮችም የመኸር ወቅት እርሻቸውን በዘር ለመሸፈን በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸው÷ የግብዓት አቅርቦት ችግር እንዲቀረፍላቸው ጠይቀዋል።
አቶ አጃክ ኡቻላም በሰጡት ምላሽ የዘር አቅርቦት ችግሩ በአጭር ቀናት ተቀርፎ ለአርሶ አደሮች እንደሚከፋፈል ተናግረዋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን፡፡