ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በኬንያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት የቀብር ስነ ስርዓት ላይ ለመገኘት ናይሮቢ ገቡ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በኬንያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት መዋይ ኪባኪ የቀብር ስነ ስርዓት ላይ ለመገኘት ዛሬ ናይሮቢ ገብተዋል፡፡
ፕሬዚዳንቷ ጀሞ ኬንያታ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም የኬንያ ስፖርት፣ ባህል እና ቱሪዝም ካቢኔ ጸሃፊ አምባሳደር አሚና መሃመድ እና በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ አለም አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
የኬንያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት መዋይ ኪባኪ የሽኝት መርሃ ግብር በነገው ዕለት የሚፈጸም መሆኑን በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይም የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።