የተለያዩ ሚኒስትሮችን ያካተተ ልዑክ የ”ፊቼ ጨምባላላ” በዓል ላይ ለመታደም ሀዋሳ ገባ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዛሬ እና ነገ በሚከበረው የፊቼ ጨምባላላ በዓል ላይ ለመታደም የተለያዩ ሚኒስትሮችን ያካተተ የልዑካን ቡድን ሀዋሳ ከተማ ገባ፡፡
ልዑኩ፥ የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የፕላን እና ልማት ሚንስትር ዶክተር ፍፁም አሰፋን እና የሴቶችና ሕፃናት ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ያካተተ ነው፡፡
የልዑካን ቡድን አባላቱ ሀዋሳ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ÷ የሲዳማ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ በየነ ባራሳና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
የፊቼ ጨምባላላ በዓልን ለማክበር የተለያዩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ወደ ሀዋሳ ከተማ እየገቡ መሆኑን ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡